የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መልዕክተኛ ሴናተር ክሪስ ኩንስ በኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ እንደሚኖር አመለከቱ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መልዕክተኛ ሆነው ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ በኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ እንደሚኖር የሚያመላክቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውን አመለከቱ።
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዲወያዩ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተላኩት ሴናተሩ፣ የጉዟቸውን ውጤት በተመለከተ ትናንት ለሴኔት አቅርበዋል።
ሴናተሩ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሌሎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር የነበራቸው ቆይታ መልካም እንደነበር በመግለጽ፣ ምስጋና አቅርበዋል።
ጉዟቸው በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ትልቅ መሻሻል እንዳለ የተመለከቱበት እጅግ ወሳኝ እንደነበር አስረድተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ዝግጁነት እንዳለ በመግለጽ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር ያሳዩትን የመንግስት ቁርጠኝነት በአብነት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ በድርድር ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት በተመለከትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ቀጣይነት ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ፣ ቀውሱን ለመፍታትና ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ እንዲሆን እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን እንደተገነዘቡም ተናግረው፣ እንቅስቃሴው የሚደነቅና ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑንም አስረድተዋል።