ያለፉት ሦስቱ የኢትዮጵያ መሪዎች ለዛሬው የሕዳሴ ግድብ የምሥራች መሠረት ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የካቲት 13/2014 (ዋልታ) ያለፉት ሦስቱ የኢትዮጵያ መሪዎች ለዛሬው የሕዳሴ ግድብ የምሥራች መሠረት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዛሬው ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራን በይፋ ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይህንኑ በተመለከተ በጉባ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

“ዛሬ እንደወትሮው ንግግር ለማድረግ አንደበት የለኝም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ንግግራቸው ምስጋና ላይ ያተኮረ መሆኑን በማስታወስ ጀመረዋል።

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን በማመስገን ንግግራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በዚያን ጊዜ ማድረግ የሚያስቸግር ቢሆንም መልካም ዘር ለልጆቻቸው አስቀምጠዋል፤” ብለዋል።

‘ቀጣዩ ትውልድ ይገነባዋል’ የሚል እምነት ይዘው የሕዳሴ ግድብን ማስጀመራቸውን ጠቅሰው፣ “ያ ሕልም በልጆቻቸው እውን ሆኗል፤ በልጆቻቸው በመተማመናቸው ምስጋና ይገባቸዋል” ነው ያሉት።

ከእርሳቸው በመቀጠል የእርሳቸው ልጅ የሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታው እና አካባቢው ምቹ እንደሆነ አምነው የሕዳሴውን ግድብ ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።

አቶ መለስ ከእርሳቸው የሚቀጥሉ ትውልዶች እንደሚጨርሱት አምነው ግድቡን በማስጀመራቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ግድቡን ተረክበው እስከ ነበረበት ስላደረሱም አመስግነዋል።

በተለይ እርሳቸው በነበሩበት ወቅት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም የሕዳሴው ግድብ በተቻለ መጠን ወደ ፊት እንዲራመድ በማድረጋቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

“ዛሬ ከእኛ ጋር ሆነው ይህን ድል በማየታቸውም እንኳን ደስ ያለዎ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል።

እነዚህ ሦስቱ መሪዎች የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም፣ የትውልድ ቦታ እና የፖለቲካ አመለካከት ሳያግዳቸው ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተቀባብለው እዚህ በማድረሳቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የጀመሩትን አመስግኖ ማለፍ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም ወሳኝ በመሆኑ እነርሱን ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ከሦስቱ መሪዎች በኋላ ሌሎች የተለያዩ አካላትን አመስግነዋል።

የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉትን ዓለማየሁ ተገኑን እና ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን አመስግነዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ አመራሮች የነበሩ ዶ/ር ምህረት ደበበ፣ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እና አሁን ያሉት የመብራት ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን አመስግነዋል።

የሕዳሴውን ግድብ የመሩት ሁለቱ ኢንጂነሮች – ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እና ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተመስግነዋል።

ከጅማሮው አንስቶ የሥራ አመራር ቦርድ ሆነው ያገለገሉ በተለይ ዶ/ር አብረሃም በላይ እና አቶ ግርማ ብሩ ከተመሰገኑት መካከል ናቸው።

በተለይ ደግሞ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተሳተፉ ሠራተኞች ሥራውን ስለሠሩ ብቻ ሳይሆን ከወራት በፊት በገጠመን ጦርነት የሕዳሴ ግድብ ለአፍታም የሚቆም ከሆነ ‘ሥራውን አቁመን ጦርነቱን እንቀላቀላለን’ በማለት የቁርጥ ቀንም አለኝታ መሆናቸውን ያሳዩ በመሆኑ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የፀጥታ ኃይል አባላት በሙሉ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያኖሩት አሻራ ትልቅ በመሆኑ አመስግነዋል።

የዳያስፖራ አባላት ገንዘብ ከማቅረብ ጀምሮ ለሀገራቸው ድምፅ በመሆን፤ በተለይ በሕዳሴ ግድብ ላይ ባሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

በግል ፍላጎታቸው የሀገራቸው ድምፅ የሆኑ፣ በተለይ በሕዳሴው ግድብ ላይ በዐረብኛ ቋንቋ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉትን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስላመነን እና ድምፅ ስለሆነን፤ ይህ ግድብ የአንድነት ዓርማ መሆኑን በማሳየቱ ምስጋና ይገባዋል ማለታቸውን ኢብኮ ዘገባ አመልክቷል።

በመጨረሻም ከሁሉም በላይ የዚህ ሁሉ ስኬት አባት የሆነውን ፈጣሪያቸውን ከልብ እንደሚያመሰግኑ ተናግረዋል።