ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር የተሰኘው ዓመታዊ ሲምፖዚየም ሊካሄድ ነው

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከዋልታ ቴሌቪዝን ጋር በመተባበር በየዓመቱ ነሐሴ 13 የሚከበረውን የቡሄ ወይም የደብረታቦር በዓል ምክንያት በማድረግ የሚከበረው ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር የተሰኘው ሲምፖዚየም ለአራተኛ ጊዜ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሊካሄድ ነው፡፡

ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር በሚል ስያሜ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበረው ክብረ በዓል ዘንድሮ በተለየ ድምቀት እንደሚከበር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ተሻገር (ፒኤችዲ) ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባህል ጥናት ዳይሬክተር እርጥባን ደሞዝ በበኩላቸው በዓሉ ላለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ የባህል ጥናት ውጤቶች ሲምፖዚየም በማዘጋጀት ዩኒቨርሲቲው ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው ባለፈው ዓመት የነበረው ፕሮግራም ትሕነግ በአካባቢው ባካሄደው ወረራ ምክንያት መቀዛቀዝ ታይቶበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዓሉ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ በድምቀት እንደሚከበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ የባህል ጥናት መጎልበት የሚያደርገውን አበርክቶ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው የበዓሉ አከባበር ላይም በባህል ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች ከፌዴራል እና ከክልል የተውጣጡ እግዶች በተገኙበት እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡