ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለ21ኛ ጊዜ 3 ሺህ 725 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን፣ በደቡብ ክልል የምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የባህል ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንዲሁም ሌሎች የክልልና የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ተማሪዎች ከዘጠኝ ወራት በፊት የተከሰተውና በአለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ተቋቁመው ለዚህ ስኬት በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው የገፅ ለገፅ ትምህርት ለወራት ተቋርጦ ቢቆይም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተማሪዎች ካሉበት ሆነው በተለያዩ አማራጮች ታግዘው የተሰጣቸውን ትምህርት መከታተላቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ሴሚስተር በቅድመ ምረቃ 58፣ በድህረ ምረቃ 44 እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ 5 ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው፣ ተማሪዎች የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁመው ለዛሬ የምረቃ ቀን በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልፀው፣ ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ ለማስቀጠል ተማሪዎች በተመደቡበት የስራ መስክ ጠንካራ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ስራዎች ላይ በማተኮር እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዋልታ ያነጋገራቸው ተመራቂ ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው መደሰታቸውንና ለሰላም፣ አብሮነት እና ለሀገራዊ ዕድገት በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
(በሳሙኤል ዳኛቸው)