ዲፕሎማሲያዊ መስመሩን ያልጠበቀው የአሜሪካ ጫና

መስከረም 11/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ ጫና ዲፕሎማሲያዊ መስመሩን ያልጠበቀና የተሳሳተ አካሄድ ነው ሲሉ የትዴፓ ሊቀመንበርና የኅዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ድርጊቱ ለማንም የማይጠቅም፤ ጫና አሳዳሪዎቹን ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገሪቱ ላይ ጫና ማሳደር የሚያስችሉ ማዕቀቦች ለመጣል የሚያደርጉት ጥረት ከዚህ ቀደም የሕወሓት አመራሮች በሥልጣን ላይ እያሉ ምን ያህል ይጠቅሟቸውና ይላላኳቸው እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡

ይህን ያልተገባ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መደበኛው የዲፕሎማሲ መስመር ብዙም ስላልረዳቸው መደበኛ ባልሆነ ዲፕሎማሲ አገሪቱ ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ቀደም ሲልም ሆነ ሰሞኑን የወሰነው ማዕቀብ እንዲጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡