ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያሰችል ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።
የስትራቴጂው ፋይዳ እና በቀጣይ አተገባበሩ ዙሪያ ላይ ከዳኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በፍትህ አሰጣጥ ሂደት የትውውቅ አሰራር፣ ጉቦና የመሳሰሉት ብልሹ አሰራሮች ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የዳኞች አገልግሎት አሰጣጥ ከሙስና ተግባር የፀዳ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው አንዳንድ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎችና የፍርድ ቤት ሰራተኞች በሙስና ፍትሕ እንዲዛባ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጸም ሙስና በተገልጋዩ እና ፍትሕ ፈላጊው ላይ ተስፋ እያሳጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቷ የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ በማውጣት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ በማጽደቅ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው እንዲሆን ለማስቻል ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ዳኞች የዳኝነት ሙያ ከፍተኛ ሥነ ምግባርን መላበስ እና ለማኅበረሰቡም ተምሳሌት መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ለዚህ ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።
ለስትራቴጂው ትግበራ አጋዥነት በሚቀጥሉት ሳምንታት በዳኞች ውይይት የሚደረግ እና ግብአቶች የሚሰበሰቡ ሲሆን በቀጣይም የስትራቴጂው ትግበራ የሚከናወን መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።