“ድፌንድ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ግብረ ኃይል በአውሮፓ ተቋቋመ

“ድፌንድ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ግብረ ኃይል

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – “ድፌንድ ኢትዮጵያ” ወይም ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም የሚል በአውሮፓ አንዳንድ የፓርላማ አባላትና መንግስታት እያስተጋቡ ያሉትን የተዛቡ መረጃዎች ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቋመ፡፡

ግብረኃይሉ ከዚህ በተጨማሪም በዲፕሎማሲ እና በሎቢ፣ በማህበራዊና በአለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለውን ሀሰተኛ መረጃ ለማረምና በሎጅስቲክስ ማሰባሰብ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡

እንዲሁም ግብረ ኃይል በመንግስት ላይ ያነጣጠሩ አሉታዊ ጫናዎችን በመቀነስ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ሁለገብ የለውጥ ሂደት ለማገዝ ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከሰባ በላይ ከፍተኛ ምሁራንና ወጣት የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን አሰባስቧል፡፡

በአውሮፓ ደረጃ ተጠናክሮ እና ተቀናጅቶ ቢቀጥል የፓርላማ አባላትን፣ ቲንክ ታንክ ቡድኖችን እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በቀላሉ ለመቀነስ ይቻላል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያዊያኑና እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በበኩላቸው፣ የዲጂታል ዲፕሎማሲና የሎቢ ዘመቻው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ቃል ገብተው የዘመኑ መረጃ ፈጣን እና ጊዜን የማይጠይቅ በመሆኑ ሳያቋርጥ መረጃ ሊያቀብል የሚችል ማዕከል እንዲፈጠር መጠየቃቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡