ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በጎዋዳሞ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጡ

ሰኔ 14/2013 (ዋልታ) – በአለታ ጩኮ ወረዳ ሰንተሪያ የምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ሆነው የሚወዳደሩት የፕላን ኮሜሽን ሚኒስተር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በማለዳ ጎዋዳሞ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዉ አረንጓዴ አሻራቸውንም አሳርፈዋል።
የህዝቡን ተነሳሽነት ያደነቁት ሚኒስትሯ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ድምፁን መስጠቱ የዲሞክራሲያዊ ስር ዓት ማሳያ በመሆኑ ውጤቱም ሲታወቅ ህዝቡ በዚህ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመሳሳይም በአለታ ጩኮ የምርጫ ክልል በ02 ምርጫ ጣቢያ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተወዳዳሪ የሆኑት የፌዴራል ዳያስፖራ ኤጀንሲ ኃላፊ ሰላማዊት ዳዊትም ድምፃቸውን የሠጡ ሲሆን ምርጫው ግልፅ ፍትሀዊ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል። የህዝቡንም ተሳትፎ አድንቀዋል።
በክልሉ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች የክልላዊና የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ለማግኘት ይፎካከራሉ።
መራጩ ህዝብም ፓርቲዎቹ ካቀረቧቸው 805 እጩዎች መካከል ለመረጠው ድምጹን እየሰጠ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ በ2, 232 የምርጫ ጣቢያዎች ለእጩዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት እየተከናወነ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት የፌደራሉ አስረኛ ክልል በመሆን የተደራጀው የሲዳማ ክልል አገራዊ ምርጫ ሲያካሂድ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።
በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በመራጭነት መመዝገባቸውን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
(በድልአብ ለማ)