“ጁንታው መበስበስ እንጂ ማበብ አይፈልግም” – የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች

ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – “አንድ ሆነን ድምፃችንን እናሰማለን፤ አንድ ሆነን ጠንካራ ክንዳችንን እንሰነዝራለን!” በሚል መሪ ቃል ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ሴቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ።
የከተማዋ ሴቶች አሸባሪው መበስበስ እንጂ ማበብ አይፈልግም ያሉ ሲሆን አከባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆማቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ ጁንታው ኢትዮጵያን ያለ ልክ በመካድ እና ሀገር የመከፋፈል ዓላማ አንግቦ እያደረገ ባለው ጦርነት እኛ ሴቶች የትኛውንም መስዋዕትነት ቢያስከፍልም ወደኋላ የማንል መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
አድዋን የደገመች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ከምን ጊዜውም በላይ አከባቢያችንን በመጠበቅ ረገድ የድርሻችንን መወጣት አለብን ያሉት ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ድል እየነሳ ያለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላትን የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
ጁንታውና የትግራይ ተወላጅ አንድ እንዳልሆኑ የገለጹት የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አሁን ያለው ጦርነት የኢትዮጵያን አንድነትና ልማት በማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች በእጅ አዙር የሚደረግ ጦርነት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በእህትማማችነት መንፈስ በያለንበት የድርሻችንን ሚና መወጣት ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ወቅት ማለፍ እንችላለን ብለዋል።
እኛ እያለን ልጆቻችን ሀገር አያጡም ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪ የህወሓት ቡድንን ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመሰለፍ ኢትዮጵያ ለማዳን ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የውይይቱ መድረኩ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁ ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡