ጁንታው የማይካድራ ዓይነት ጭፍጨፋ በሑመራ ከተማ ለመፈጸም ያሰበው ዕቅድ ተጋለጠ

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – ጁንታው የህወሓት ቡድን የማይካድራ ዓይነት ጭፍጨፋ በሑመራ ከተማ ለመፈጸም ያሰበው ዕቅድ ተጋለጠ፡፡
በዕቅዱ መሠረት ከትግራይ ክልልና ከሱዳን አስርጎ በሚያስገባቸው ሠርገ ገቦች አማካኝነት ጭፍጨፋውን እንደሚፈጽም ገልጿል።
ይሄንን ለማድረግ እንዲመች በራያና አፋር በኩል ተደጋጋሚ ትንኮሳ በመፈጸም የመከላከያ ሠራዊቱንና የአማራ ልዩ ኃይልን ትኩረት ለማዛባት ሞክሯል።
የጦር ኃይል ወደ ራያና አፋር ሲሰባሰብና የምዕራቡ ኃይል ሲሳሳ በዚያ በኩል ጥቃት በመክፈት ድርጊቱን ለመፈጸም ማቀዱን ያሳያል።
ጁንታው ከሰሞኑ የአማራ ልዩ ኃይልና መከላከያ በሑመራ ጭፍጨፋ እንደሚፈጽሙ በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨት እንደሚጀምር ዕቅዱ ያሳያል ሲል የመንግስት የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ማስጠንቀቂያ 1 በሚል ባወጣው ጽሁፍ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ጁንታው ከሰሞኑ በአፋር ግንባር በፈጠረው ትንኮሳ ከአፋር ልዩ ኃይልና ከመከላከያ ሠራዊት ምላሽ ተሰጥቶታል ሲል የመረጃ ማጣሪያው አስታውቋል፡፡
በዚህ ትንኮሳ ወቅት ያሰለፋቸው ያልሠለጠኑ ሕጻናትና ሴቶችን መሆኑ ታውቋል።
ጁንታው ከአካባቢው ሲሸሽ ከ300 በላይ አስከሬኖች በሲኖ ትራክ ጭኖ ወደ መቐሌ መፈርጠጡ ታውቋል።
የደኅንነት ምንጮች እንደጠቆሙት ጁንታው በዚህ መልክ የሚያሸሻቸውን የሕጻናትና የሴቶች አስከሬኖች በአንድ መቃብር በመቅበር የጅምላ ግድያ የተፈጸመባቸው መቃብሮች አስመስሎ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው ሲል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ማስጠንቀቂያ 2 ባለው መረጃ አስታውቋል።