ጃፓን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም ሂደት አደነቀች

የካቲት 21/2015 (ዋልታ) ጃፓን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም ሂደት፣ መልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ስራ እንደምታደንቅ ገለጸች፡፡

የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የጃፓን የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሰይዳ ሺኒቺ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለማምጣት ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሟን አስረድተዋል፡፡

የጃፓኑ አምባሳደር ሰይዳ ሺኒቺ በበኩላቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ እያደረገች ለሚገኘው መልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ስራ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡