ጄነራል አብዱል ፈታህ በሱዳን የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ አዘዙ

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በአገሪቱ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ አዘዙ፡፡

የአገሪቱ የሉዓላዊ ምክር ቤት ትላንት በሰጠው መግለጫ ጄነራል አብዱል ፈታህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚያነሳ አዋጅ ማውጣታቸውን አስታውቋል። ይህም ፍሬያማ እና ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህግ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ውሳኔው የተላለፈው የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ተወካይ ቮልከር ፔርቴስ ባለፈው ቅዳሜ በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ሁለት ተቃዋሚዎች መገደላቸውን ተከትሎ ባቀረቡት ጥሪ ጄነራሉ ከአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተው ነው ተብሏል።

ሱዳን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በሕዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች ስትሆን በአመጽ የተወሰደ እርምጃ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት አልፏል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ታስረዋል፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 25/2021 በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሱዳን በከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ስትታመስ ቆይታለች። ይህም የምዕራባዊያን መንግሥታት ወሳኝ የእርዳታ ቅነሳን ጨምሮ ሰፊ ዓለም ዐቀፍ ውግዘትን እና የቅጣት እርምጃዎችን እንድታስተናግድ አድጓታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት፣ አፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ በጋራ ቀውሱን ለመፍታት ውይይት እንዲመቻች ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውም ይታወቀል፡፡

የጦር አዛዡ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንም የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት እና የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት ቃል ገብተዋል ሲል ኔሽን አፍሪካ ዘግቧል፡፡