ገዳ ባንክ የመስራቾች ጉባኤ አካሄደ

ሐምሌ 29/2013(ዋልታ) – በ500 ሚሊዮን ገቢ በሆነ የባለአክሲዮኖች መዋጮ እና 1.3 የተመዘገበ አክሲዮን የተመሠረተው ገዳ ባንክ የመስራቾች ጉባኤ አካሄደ።

ባንኩ ከምስረታው በገዳ ስረዓት የሚመራ እንደሆነ የተነገረለት የገዳ ባንክ በሁሉም የስራ መስክ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ይሆናል ነው የተባለው።

በገዳ ስረዓት አቃፊነት መገለጫው ነው ያሉት አባ ገዳዎች ገዳ ባንክም በዚሁ መሠረት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እና ከ27 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ባንኩ በመላው የሀገሪቷ ክፍል ውስጥ በመንቀሳቀስ ለመስራት አቅዷል።

በተለይም በልማት ምክንያት የካሳ ክፍያ ተከፍሏቸው ከቦታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮችን ማእከል በማድረግ ይሰራል ነው የተባለው። እነዚህ አርሶ አደሮች ለዘመናት ያፈሩት ቤት እና ንብረት በልማት ምክንያት የካሳ ክፍያ ተከፍሏቸው እንዲነሱ ሲደረግ ራሳቸውን መልሰው እንዲያቋቁሙ የስልጠና እና ሌሎች ድጋፎች ስለማይደረግላቸው ወደ ከፋ ድህነት ውስጥ ይወድቃሉ።

ይህን ታሪክ ለመቀየር እሰራለው ያለው ገዳ ባንክ እስካሁንም ባደረገው እንቅስቃሴ ከ8000 በላይ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ማግኘቱን እና እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ አክሲዮን የገዙ መኖራቸውን አቶዋሲሁን አመኑ የባንኩ መስራች አስተባባሪ ኮሚቴ ተናግረዋል።

በምስረታ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የአዲሱ ትውልድ ባንክ ነው የተባለው ገዳ ባንክ በሀገሪቷ ያለውን የባንክ ዘረፍ ታሪክ ለመቀየር መስራት አለበት ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ስልጣን ላይ የነበረው እና በህዝብ ትግል ከስልጣን የተወገደው የሕወሀት መንግስት እንኳን እንዲህ አይነት ህዝባዊ መሠረት ያለው ባንክ እንዲቋቋም ሊፈቅድ ኦሮሚያ ባላት የተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ ህዝቦቿን እንዳታኖር የሰዶ ማሳደድ ስራ በዜጎች ላይ ያደርስ ነበር ነው ያሉት።

አሁን ከለውጥ በኋላ ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ከምንም ተነስቶ እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ነው  ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።

ታድያ ይህም ባንክ ዜጎች እንዲቆጥቡ በማድረግ የሀገሪቷ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት እንዲገባ በማድረግ የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሳደግ የራሱ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት መልክት አስተላልፈዋል።

የሀገሪቷ ክፍሎች በየገጠሩ ያለው ማህበረሰብ እንዲቆጥብ እና ህይወቱ እንዲቀየርም የክልሉ መንግስት ከባንኩ ጋር ይሰራልም ነው ያሉት ሽመልስ አብዲሳ።

የገዳ ባንክ በብሔራዊ ባንክ ህግ መሠረት አዲስ ባንክ ከተመሠረተ ግዜ አንስቶ በቀጣይ ሰባት ዓመት ውስጥ የገንዘብ አቅሙን 5 ቢሊዮን እንዲያደርስ የሚል ቢሆንም ይህን ከዛ ቀድሞ ለሟሟላት እሰራለሁ ብሏል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)