ጉዳት የደረሰበትን የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው

መጋቢት 6/2014 (ዋልታ) በምስራቅ አማራ እና በአፋር አካባቢዎች በአሸባሪው ሕወሓት የተጎዱ የፋይበር ኦፒቲክስ የአሌክትሪክ መስመሮችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ገብረ መድህን ከኮምቦልቻ – ሰመራ፣ ከሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ፣ ከኮምቦልቻ – አላማጣ እንዲሁም ከኮምቦልቻ – አቀስታ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ምሶሶዎች አናት ላይ ተዘርግተው በሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብና መመልከት አለመቻሉን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት የአማራና አፋር ክልሎችን በወረራ ይዞ በቆየባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የማስተላለፊያ መስመሮች መካከል በ53 ነጥብ 3 በመቶ ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡