ጋዜጠኞች ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) ጋዜጠኞች እና የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለጋዜጠኞች እና ለመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ማብራሪያው ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ስለምታስተናግደው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ለማህበረሰቡ የማሳወቅ ስራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጋዜጠኞች እና የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጉባኤውን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም ጫና እየተደረገብን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጋዜጠኞች ይህንን በመከላከል ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙም ነው የጠየቁት።

በውይይቱ ስለ ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ምንነት፣ ስለሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም እንዲሁም ጉባኤውን ለማስተዋወቅ መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ተነስቷል።

ጉባኤው ከኅዳር 19 እስከ 23/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ከ2 ሺሕ 500 በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW