ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የስራ ኃላፊዎች ላይ ፍርድና ብይን ተሰጠ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጌታቸው አሰፋ፣ ያሬድ ዘሪሁን እና ሌሎች 24 ተከሳሾች ላይ ፍርድ እና ብይን መሰጠቱ ተገለጸ።

ተከሳሾቹ ከ1984 እስከ 2010 ባሉት በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መስሪያ ቤት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ተመድበው ሲሰሩ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ ባሉ ክፍለ ከተሞች፣ በአማራ ክልል ባህርዳርና ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔና ቢሾፍቱ፣ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ሰዎች የሚታሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸውና ድብቅ እስር ቤቶችና መመርመሪያ ክፍሎች እንዲዘጋጁ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህም በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የመያዝ የማሰርና የመመርመር ሥልጣን ሳይኖራቸው ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥራችኋል በማለት በሌሊትና በቀን፣ ለወራትና ለዓመታት ከታሰሩበት ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ በላያቸው ላይ ውሃ እየደፉ፣ በአፍ ውስጥ ካልሲ በመክተት፣ የእግር ጥፍር በመንቀል፣ የተበዳዮችን የሰውነት ክፍል በኤሌክትሪክ በማስነዘር፣ እጅና እግርን በብረት ሰንሰለት በማሰርና ጠረጴዛ ላይ በመስቀል ሚስማር ባለው ጣውላ እንዲደበደቡ እንዲሁም በኤሌክትሪክና በሽቦ ገመድ እንዲገረፉ በማድረግ፣ ራቁታቸውን ጉንዳን ውስጥ በማስገባት፣ በብልታቸው ላይ የፕላስቲክ ውሃ በማንጠልጠል፣ በአፍንጫቸው እስክርቢቶ በመስደድ ከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰትና ሥልጣንን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ እንደየተከሰሱበት አንቀፅ ጥፋተኝነታቸው በዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞው ዳይሬክተር ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አፅበሃ ግደይ፣ አሰፋ በላይና ሽሻይ ልኡል አራት ተከሳሾች በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ብይኑን የተከታተሉ ሲሆን ተከሳሾቹ አንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በዋስ ወጥተን ክሳችንን እንከታተል ብለው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዐቃቤ ሕግ በዋስትና ጥያቄው ላይ በጽሑፍ አስተያየት ልስጥበት በማለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታኅሣሥ 6 መሰጠቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።