ግሎባል አሊያንስ ለተፈናቀሉ ወገኖች 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) ግሎባል አሊያንስ በአሸባሪው ሕወሓት ከሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደባርቅ ከተማ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 7 ሚሊዮን 5 መቶ ሺሕ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የግሎባል አሊያንስ ሊቀመንበር አርቲስት ታማኝ በየነ በአሜሪካን ሀገር በሂውስተን፣ በፍሎሪዳ፣ በፍላደልፊያና ናሽቪል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የግሎባል አሊያንስ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ለተቸገሩ ወገኖቻችን ድረሱላቸው ብለው በሰጡን ገንዘብ ድጋፉን አምጥተናል ብሏል፡፡

በዚህም 2ሺሕ 250 ብርድልብስ፣ 1ሺሕ 200 ኩንታል ዱቄትና 2 ሺሕ 200 ፍራሽ አምጥተናል ብሏል፡፡

ድጋፉ ችግሩን ይፈታል ብለን ሳይሆን ወገን እንዳላችሁ እንድታውቁ የተደረገ ድጋፍ ነው ሲል ገልጿል፡፡

የግሎባል አሊያንስ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ክፉዎች እንዳሉ ሁሉ ደጎችም ስላሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ደግ ኢትዮጵያዊያን ባዋጡት ገንዘብ ድጋፍ አምጥተናል ብለዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸው ተፈናቃይ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡