ነሐሴ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ በሰብል ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ተባዮችን እና የግሪሳ ወፍን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይነህ ንጉሴ በ2016/17 የምርት ዘመን የተዘራው ሰብል ምርታማነት እንዲጨምር የሰብል ጥበቃ ሥራ በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የበቀለው ሰብል ላይ በሽታና አረም ጉዳት እንዳያደርስ ጥበቃና እንክብካቤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ ተዛማች ተባይን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ኬሚካል መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ለኬሚካል ርጭት አምስት የርጭት አውሮፕላኖች፣ በተሽከርካሪ ላይ የተገጠሙ የመርጫ ማሽኖች እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የርጭት አውሮፕላኖች የሚያርፉበትን ሜዳ የመለየት፣ የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ቦታዎችን የማሰስ ተግባራት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሰውን የዋግ በሽታን የሚከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩም ለምርት ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ምርታማነት እንዲጨምር ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።