“ግዕዝ ወጥበባት” በሚል መሪ ሀሳብ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 27/2014 (ዋልታ) “ግዕዝ ወጥበባት” በሚል መሪ ሀሳብ ሰባተኛው የግዕዝ ጉባኤ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት፣ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የደብረ ታቡር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ጋሻ (ዶ/ር) የአንዲት ሀገር ሀብት እንዲያድግና ለትውልድ እንዲተላለፈ ቋንቋ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ግዕዝ ማለት አንደኛ ማለት ሲሆን የግዕዝ ቋንቋ ከቀዳሚዎቹ ቋንቋ ተርታ ይመደባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ይኩኖ አምላክ በበኩላቸው ዋና ዋና የቅኔ መምህራን በሚገኙበት ደብረ ታቦር መካሄዱ ሰባተኛውን የግዕዝ ጉባኤ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

ጥንታዊ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ ትልቅ የሆነ የአዕምሮ ችሎታን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ የግዕዝ ጉባኤ መካሄድ መጀመሩ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ትምህርት ክፍል እንዲያቋቁሙ እያስቻለ ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ በግዕዝ ላይ የሚያጠነጥኑ በርከት ያሉ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የተገለጸ ሲሆን ቅኔ፣ ድጓና አቋቋም ይቀርባሉ ተብሏል።

በመድረኩ የተለያዩ የቅኔ መምህራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ደምሰው በነበሩ (ከደብረ ታቦር)