ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደገፉበት ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

ግንቦት 7/2016 (አዲስ ዋልታ) የአውሮፓ ሕብረት እና አጋሮቹ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለውን ኢኮኖሚ ወደነበረበት መመለስ እና አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችላቸውን ፕሮግራም ይፋ አድርገዋል።

ፕሮግራሙ በሰሜን ኢትዮጵያ ከግጭት በኋላ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት ለመደገፍ ዓላማ ያደረገ ሲሆን ይህም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎችና በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን በመደገፍ ወደ ምርትና ምርታማነታቸው ለመመለሰ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን ሙሀመድ የአውሮፓ ሕብረት፣ ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ቀጣይነት ባለው መልኩ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው ይህም በሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ልዩ ጠቀሜታ አለው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ ኢኮኖሚ እንዲያገግም በማድረግ እና ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡