ጠ/ሚ ዐቢይ በዩክሬን ቀውስ ውስጥ ሁሉም ወገኖች ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጠየቁ

ጠ/ሚ ዐቢይ

የካቲት 24/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዩክሬን ቀውስ ውስጥ ሁሉም ወገኖች ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዩክሬን የተፈጠረውን ቀውስ አስመልክተው በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በቅርቡ ካለፈችበት ጦርነት ተነስታ ስለጦርነት ጉዳት የምታካፍለው ሰፊ ልምድ እንዳላት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ልምድ ጦርነት ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚን ክፉኛ የሚጎዳ አጥፊ ነው ብለዋል።

ጦርነት የሚያደርሰውን ቁሳዊ ጉዳት መጠገን ቢቻልም በማኅበረሰብ ላይ ጥሎት የሚያልፈውን ጠባሳ ግን ለማከም ከባድ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ወቅታዊውን የዩክሬን ቀውስን በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግጭቱን የሚያባብሱ ሁኔታዎች እንደሚያሳስባትም ገልጸዋል።

በመሆኑም ሁሉም ወገን ቀውስን ከሚያባብስ ድርጊት ታቅቦ ግጭቱን ለመፍታት ሁለንተናዊ የሰላም መንገዶችን እንዲጠቀሙ ጠይቀው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን ምኞትም በጽሑፋቸው አስፍረዋል።