ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከአውሮፓ ኅብረት አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ተገለጸ

የካቲት 10/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከኅብረቱ ዓለም ዐቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር በብራስልስ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

በውይይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለኅብረቱ አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በመንግሥት በኩል የተለየዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ማስታወሳቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን መንግሥት ያደረጋቸውን ጥረቶች ማብራራታቸውንም ገልጸዋል።

መንግሥት በርከት ያሉ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም አሸባሪው ሕወሓት ግን አሁንም በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ንጹሃን ዜጎችን ለሞት እየዳረገ፣ ብዙዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ መሆኑን ጭምር እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው::