ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ጊዜው የኅዳሴው ግድብ ለሶስቱ አገራት የሰላም፣ የትብብር እና የአብሮ መኖር ተምሳሌትነቱን የምናሳይበት ነው አሉ

ጥር 12/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጊዜው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የሰላም፣ የትብብር እና የአብሮ መኖር ተምሳሌትነቱን የምናሳይበት ነው ሲሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማምረቻው ዘርፍ እና በኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ህልም ለማሳካት የምትችለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅሟን ማሳደግ ስትችል ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በማኅበራዊ ዘርፍ በኩልም ጥራት ያለው ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት እና ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለዜጎች ለማቅረብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጧም ሆነ ባላት የውኃ ሀብት ያላትን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት የውሃ ኃይሏን መጠቀም እንደሚገባትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት 53 በመቶ ወይንም ወደ 60 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ያለ ኤሌክትሪክ የትኛውም አገር ዘላቂ ልማት እና እድገት ሊያረጋግጥ አልቻለም ብለዋል።