መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት መጽሐፍ ለሚለግሱ ግለሰቦች ምስጋናዬ የላቀ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በአብርኆት ቤተ መጻሕፍት በነበረን መርሐ ግብር በእንግሊዝ ሀገረ በትምህርት ላይ የምትገኘው ወጣት ቤተልሔም ሰሎሞን 5ሺሕ 200 መጻሕፍት ከእንግሊዝ አምጥታ ማስረከቧ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አንድ ዐቢይ ኮሚቴ ያዋቀርን ሲሆን ከቀናት በኋላ ለአንድ ወር የሚቆይ የመጽሕፍት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ይኖረዋልም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንገኝ ወገኖች በመጻሕፍት ማሰባሰቢያ ወር የመጻሕፍት ልገሳ ለማድረግ እንዘጋጅ፣ ለትውልድም ዕውቀት እንድንለግስ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።