ጠ/ሚ ዐቢይ በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉት ንግግር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) በትናንትናው ዕለት አዲስ የመንግስት ምስረታ መካሄዱና ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸው ይታወቃል።

የአዲሱን መንግስት ምስረታና በዓለ ሲመታቸውን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የመንግስት ምስረታ በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉት ንግግር አድርገዋል፡፡

የንግግራቸው ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፥

ክቡራትና ክቡራን፤

በኢትዮጵያ ረጅም የመንግስት አስተዳደር ዘመን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽና ተዓማኒ ምርጫ በማካሄድ ፥ ሕዝባዊ ቅቡልነትን ያገኘ መንግሥት በምንመሠርትበት ታሪካዊ ቀን ፥ ከፊታችሁ ቆሜ ንግግር ለማድረግ ያበቃኝን ፈጣሪ ከሁሉ አስቀድሜ ለማመስገን እወዳለሁ።

በዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት በሀገራችንና በሕዝቦቿ ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ፥ በዱር በገደሉ፤ በቁር በሐሩሩ፣ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ለሚገኙት – ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ፥ ለመላው የፀጥታ አካላት እና ለሕዝባዊ ኃይላችን ያለኝን ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ልገልጽ እወዳለሁ።

እናንተ የቁርጥ ቀን ልጆች ፥ ጀግና የምታከብረው ኢትዮጵያ ውለታችሁን መቼም ቢሆን አትረሳውም።

ሀገራችን እንደቀደሙ ጀግኖቿ ለዚህ ትውልድ ፈርጦችም ትልቅ ክብርና ሞገስ ትሰጣለች።

የምትከፍሉት መስዋዕትነት በታሪክ ማሕደር እና በልባችን ብራና ላይ በደማቁ ታትሞ ይኖራል።

እልፍ ጀግኖችን ካፈራው ሕዝባችን አብራክ በመፈጠሬ ሁሌም እንድኮራ ከሚያደርጉኝ ነገሮች መካከል – የሕዝባችን ፅናት ፥አይበገሬነት እና አትንኩኝ ባይነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ሕዝባችን በየትኛውም ዘመን የእናት ሀገር ጥቃት የሚያንገበግበው ፥ ጠላትሲመጣ የግል ቅሬታውን ወደ ጎን ብሎ ሀገርን የሚያስቀድም ፥ በሉዓላዊነቱየማይደራደር ነው፡፡ በዚህም የተነሣ መተማመኛችን፥ ጦርና ጋሻችን፥ ተዋጊና ደጀናችን ለሆነው ሕዝባችን ያለኝን ክብርና

አድናቆት ልገልጽ እወዳለሁ።

በተመሳሳይ፥ ኢትዮጵያ ድጋፍ በፈለገች ጊዜ ለደረሳችሁላት ፥ ዐቅም ባነሳት ጊዜ ምርኩዝ ለሆናችኋት ፥ በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ – በሕዝብና መንግሥት ስም የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ውድ ኢትዮጵያውያን፥

ክቡራትና ክቡራን፥

ኢትዮጵያ – በአቃፊነቷና በቀደመ ገናና ታሪኳ በመርከብ ትመሰላለች።

በታላላቆቹ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረው፥ መርከቧ ኢትዮጵያ – የፍትሕ፥ የእኩልነት፥ የነጻነት እና የላቀ ስብእና ሀገር ናት። እኛ በመጽሃፍ ቅዱስ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን – ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም” የተባለልን እና ከቀደምት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን ያፈራን፤ ነብዩ መሐመድ (ዐ.ሰ.ወ) የተከታዮቻቸው ማረፊያ አድርገው የመረጧት ፤ የእውነት እና ርትዕ ሀገር ብለው ያወደሷት እናየመጀመሪያው ሙዓዚን ቢላል መነሻ የሆነች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

እኛ ማለት የመካከለኛው ዘመን ፖርቱጋላዊ አሳሽና ጸሐፊ ፔድሮ አልቫሬስ “ኢትዮጵያውያን ፍትህና ዳኝነትን የሚያውቁ፥ ኪነ ህንጻ እና ስዕሎቻቸው በጥበብ የደመቁ” ሲል የመሰከረልን ሕዝቦች ነን፤ ኢትዮጵያ በኤዞጵ ተረቶችና በሜናንደር ተውኔትዎች የተወደሰች ፥ ግሪካዊ የታሪክ አባት ሄሮዳተስ “የወርቃማ ባህልና ስነ-ምግባር ባለቤት የሆኑ ብልህ ህዝቦች” ብሎ የጻፈላት፤የዘመናችን አርኪዎሎጅስቶች ምድረ ቀደምትነቷን ያረጋገጡላት ፤ ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ-ግዛት እና ፀረ-አፓርታይድ ትግል ወቅት ከራሷ አልፋ ፥ ለአፍሪካ ነጻነት ከውስን ሀብቷ ሳትሰስት ቀንሳ የሰጠች ፤ በጥቁር ህዝቦች መብት ትግል ውስጥ ትልቅ ቦታ በነበራቸው ማርክስ ጋርቬይ እና ዱ ቦይስ ልቦና ውስጥ ጎልታ የተሳለች ፤ በማንዴላ ውብ ቃላት “አፍሪካዊ ማንነቴን የገለጠችልኝ” ተብላ የተወደሰች ፤ የእውነት እና የአፍሪካዊነት ሞገስ ነች ኢትዮጵያ።

አንዳንዶች ዛሬ “አትችሉም” ሲሉን ፤ አንድም – ከታሪክ መዝገብ ገልጠን የአባቶቻችንን ገድል በማጣቀስ ፥ አንድም – የእኛ ትውልድ ለኢትዮጵያ ብልፅግና የወጠነውን አይቀሬ የተግባር ጉዞ ወደ ውጤት በመቀየር መቻላችንን ልናረጋግጥ ይገባል። በቀደሙ ድሎቻችን ከሚሰማን የኩራት ስሜት ጋር ሲነጻጸር ፥ ነገ ላይ የሚጠብቀን ተስፋ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ዋናው ጥያቄ – ተስፋውን አይተን እውን ለማድረግ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን? የሚለው ነው። ኢትዮጵያ የምትበለፅገው እኛ ሀገራችንን ለመለወጥ በፈለግንበት መጠንና የጋራ ራዕይ በሰነቅንበት ልክ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ካዘመመችበትቀና የምትልበትጊዜው አሁን ነው፡፡ ይኼን ለማሳካትየዛሬ ሕያው ኢትዮጵያውያን ታላቅ አደራ ተጥሎብናል። ይሄንን አደራ ጠብቀን ፤ የዘመናት በጎ ድምር ውጤቶችን አጎልብተን ፥ ኢትዮጵያ የተባለችውን መርከብ ሞተሯን አድሰን ፥ ማዕበልና

ወጀብ ፈጽሞ እንዳያናውጣት አንጸን ፥ መልሕቋን አንስተን ፥ ጉዞዋን ማስጀመር የእኛ ድርሻ ሲሆን ፤ ለዘለቄታው በጽናት እንድትጓዝ ማድረግ ደግሞ የየትውልዱ አደራ ይሆናል።

ውድ ኢትዮጵያውያን፥

ክቡራትና ክቡራን፥

ሀገራችን፥ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት ዴሞክራሲን በሥርዓተ መንግስቷ ለመትከል ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጋለች። ተስፋና ስጋት ፥ ዕድልና ፈተና እየተፈራረቁባት አያሌ ውጣ ውረዶችን ተሻግራ እዚህ ደርሳለች። የማንነት፥ የእኩልነት፥ የነጻነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች – ከአርሶ አደር እስከ አርብቶ አደር ፥ ከከተሜ እስከ ባላገር ፥ ከመለዮ ለባሽ እስከ ምሁር ፥ ከወጣት እስከ ጎልማሳ ፥ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ፥ መላው የሀገራችን ሕዝቦች የተሳተፉበትና መሥዋዕትነት የከፈሉበት የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ ነበር። ምንም እንኳን 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከእንከኖች ሁሉ የፀዳና የምኞታችንን ያህል እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም ፥ የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመትከል እና የማፅናት ሕልም ዕውን ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ፤ አንድ እርምጃም ወደፊት አራምዶናል።

ሥልጣን ከዘር ሃረግ ወይም ከጠመንጃ አፈሙዝ ፥ አልያም በሴራና ተንኮል ሳይሆን ፤ በእውነተኛ የሕዝብ ድምፅ ከምርጫ ኮሮጆ ብቻ የሚመነጭ በማድረግ ፤ የሕዝብን የፖለቲካ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ያረጋገጥንበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ሕዝባችን – የዕንቅፋት ክምር ሳያስቆመው ፥ በጊዜያዊ ፈተና ተስፋ ሳይቆርጥ ፥ በልዩ ልዩ ሰው ሰራሽ ግጭቶች ሳይረበሽ ፥ እንደ ኮቪድ ወረርሽኝ ባሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳይበገር ፥ በሀገራዊ ሉዓላዊነታችን ላይ በተጋረጠው አደጋ ሳይረታ፥ ከውጪ ኃይሎች በሚደርስበት ተፅዕኖ ሳይንበረከክ ፥ በሂደቱ የገጠሙትን እንከኖች ሁሉ ተጋፍጦ ፥ የዜግነት ድርሻውን አኩሪ በሆነ መልኩ ተወጥቷል።

ውድ የሀገሬ ልጆች

ክቡራትና ክቡራን፥

በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም፤ የመንግስትም ብቻ አይደለም። ድሉ – ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፥ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ በአንድነት ያሸነፍንበት መሆኑንን ተገንዝበን ፤ ይሄን አጋጣሚ እንደ ሀገር በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ካዋልነው ብዙ ቀዳዳዎችን መድፈን የሚያስችል ትልቅ እድል ነው።

ለዘመናት እየተከማቹ የመጡትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ፥ በአንድ ፓርቲ መሪነት እና መፍትሔ አፍላቂነት ጨርሶ ማስወገድ እንደማይቻል ታውቆ ፥ ተደራርበው የመጡብንን ችግሮች ተባብረን እና ተደምረን ለማሸነፍ መነሳት ይኖርብናል። በእኛ በኩል – በሁሉም ፥ ከሁሉም ፥ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ሕልም ለስኬት እንዲበቃ – አሳታፊና አካታች አካሄድ ለመከተል አጥብቀን እንሠራለን። የፖለቲካ ሥርዓታችን የአሸናፊዎች ፍላጎት ነጸብራቅ ብቻ ሳይሆን የመግባባታችን ውጤት እንዲሆን አበክረን እንሠራለን። በታሪካችን ውስጥ በጉልህ እንደሚታየው ፥ የውስጥ ሽኩቻዎቻችን ለጠላቶቻችን መሳለቂያና መረማመጃ

አድርገውን ቆይተዋል። የኦሮሞ አባቶች “Waliigalan alaa galan” ይላሉ። “የተግባባ ከውጪ ይገባ፤ የተነጋገረና የመከረ ለአንገብጋቢ ችግሮቹ መፍትሄ ያገኛል” እንደማለት ነው። በመጪው ዘመን ብዝሃነታችንን በጌጥነት ተቀብለን ፥ መታረቅ የሚችል ሀሳባችንን አስታርቀን ፥ መከበር የሚገባው ልዩነታችንን አክብረን ፥ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረን ፥ ወደ ከፍታ የምንተምበትጊዜይሆናል፡፡ ይህም እንዲሳካ የፖለቲካ ልዩነታችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን። የምክክር ሂደቱ – ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙርያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን የሚያካትት ፥ በፖለቲካ ልሂቃን መካከል የሚደረግ ሂደት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያገናዘበ ፥ አጠቃላይ ሂደቱ አካታች እና አሳታፊ ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን እየተመራ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ለማፍለቅ ታልሞ የሚከናወን ይሆናል።

ውድ ኢትዮጵያውያን፥

ክቡራትና ክቡራን፥

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በክህደት እና በእብሪት የተጠነሰሰው ግጭት ባሳለፍነው ዓመት እንደ ሀገር እጅግ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል። ይህ ግጭት ጥቂት ግለሰቦች “እኛ የማንቆጣጠራት እና እንዳሻን የማናሾራት ሀገር ልትኖር አይገባም” ብለው የቀሰቀሱት ጦርነት ነው። ጠላት በአሽከሮቹና አሳዳሪዎቹ እየታገዘ ብረት አንስቶና አውዳሚ መሳሪያዎችን ታጥቆ ፤ እንደ ብሌናችን የምንሳሳለት የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የግፍ ግፍ ፈጽሟል።

በቅርቡ እንኳን የጥሞና እድል ብንሰጠው፥ ክፉ ደጉን ያልለዩ ሕፃናትን የጦር መሳሪያ አስታጥቆ፥ የሕዝብ መገልገያዎችን እየናደ ፥ ትምህርት ቤትና ጤና ኬላዎችን እያፈረሰ ፥ ቤተሰብ እየበተነ ፥ ንጹሐንን እየረሸነ ፥ አርሶ አደሩ ከልጆቹ ለይቶ የማያያቸውን ከብቶቹን በጥይት እየገደለ ፥የሐይማኖት ተቋማትን እያረከሰ ፥ ኢትዮጵያን ሲወጋት ፥ ወደን ሳይሆን ተገደን ሕልውናችንን ወደ ማስጠበቅ ዘመቻ መግባታችን ሊታወቅ ይገባል። ሰልፍ ይዘን ስንዘምትም ሆነ ሰይፍ ይዘን ስንነሳ ፥ ዋና ጸባችን ሀገር ሊያፈርሱ ፥ ሕዝብ ሊያናክሱ ፥ ወንበራቸውን ሊያደላድሉ ፥ ኪሳቸውን ሊሞሉ ከተነሱ የሴራ ቁንጮዎች እና ኢትዮጵያ-ጠል ኃይሎች ጋር ብቻ ነው። ሀገራችን ከውጭና ከውስጥ የገጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ለማለፍ እና በቀጣይም ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር እንድትችል ትክክለኛ አቋም እና የተሟላ አቅም ያለው የፀጥታና ደህንነት ኃይል ትገነባለች።

ክቡራትና ክቡራን

ሉዓላዊነታችንን እና የግዛት አንድነታችንን የሚገዳደረውን ክፉ መሻት በምንከላከልበት በዚህ ወቅት፥ ከዓለም አቀፍ ኃይሎች እያስተናገድን ያለው የዲፕሎማሲ አዝማሚያ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን እንድንገልጥ አስገድዶናል። በዘመናት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ሐቆችን አሳልፈናል። ዛሬም እንደ ትላንቱ የወዳጅነትን ታሪክ የቀጠሉ እንዳሉ ሁሉ፥ የክህደትን ታሪክ የደገሙም አሉ። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት አጥብቃ ትሻለች። ነገር ግን ማንኛውም ወዳጅነት የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት በሚሰዋ መልኩ መሆን የለበትም፤ ሊሆንም አይችልም።  በፍቅርመንፈስ ለሚቀርቡን ሀገራት ልባችንና በራችን ለድጋፋቸው፥ ለምክራቸውና ለመልካም ምኞታቸው ሁሌም ክፍት ነው።

ውድ አፍሪካዊ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን፥

እኛ ኢትዮጵያውያን “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል መርህ የተባበረች ፥ ሰላማዊና የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት ብሎም፥ በዓለም መድረክ ጥቅሟን የምታስጠብቅ አህጉር እንድትኖረን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንጥራለን።

በቀጣናችን – ከሚያጋጩን ይልቅ የሚያስታርቁን፥ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያስተባብሩን ነገሮች ብዙ ናቸው። የጋሞ አባቶች “ከሰው ጋር አንድ ዓመት ያላረሰ፤ ለብቻው ሰባት ዓመት ያርሳል” እንዲሉ፤ እጣ ፈንታችን የተሳሰረ ስለሆነ፥ በቀጠናችን ያለውን የተበታተነ ዐቅም ሰብሰብ አድርገን ብንተባበር ያሉብን ችግሮች “በንስር ፊት እንደቆመች ድንቢጥ” ይኮሰምናሉ።

ክቡራትና ክቡራን፥

የሕዳሴ ግድብ እንደ ሀገር ከሚያስገኝልን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር፥ ቀጣናዊ ትሥሥር እና መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የአባይ ወንዝ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳነቱ ባለፈ ተምሳሌታዊ ትርጉሙ ግዙፍ ነው። አባይ ማለት – የመነሳታችን ምሳሌ ፥ በራሳችን አቅም የመቆማችን ማሳያ ፥ የሕብረታችን ገመድ ነው። አባይ በማይታይ ምትሐቱ ስላስተሳሰረን ፥ በማይዳሰስ ኃይሉ ስላበረታንና በራስ መተማመናችንን ስለጨመረ ፥ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ፥ ከከተማ እስከ ገጠር ፥ ከቆላ እስከ ደጋ ፥ ከደቡብ እስከ ሰሜን ፥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ፥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዕለት ጉርሱና ከመንፈቅ ልብሱ ቀንሶ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቆርጧል። ጎረቤቶቻችንና የአባይ ልጆች ይኼንን ሀቃችንን እስከተረዳችሁልን ድረስ፥ በአባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ፥ ቀጠናዊ

ትስስርን በሚያጠናክር እና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ነን።

ውድ የሀገሬ ልጆች፥

ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ጎዳና የማሸጋገር ውጥናችንን ወደ ውጤት ለመቀየር ኢኮኖሚያችን በብዝሃ ዘርፎች የተዋቀረ ፥ ብዝሃ ተዋናይ የሚሳተፍበት እና ብዙዎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ እንሠራለን። ኢኮኖሚያችን በግል ዘርፍ ቀዳሚነትና ገበያን በሚደግፍ መንግስት አጋዥነት የሚመራ ፥ ተወዳዳሪ እና ከዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር የተሳሰረ ፥ ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ፥ ለዜጎቻችን በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ምጣኔ ሀብት እንዲሆን እንሰራለን። ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠርና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንፃር የተወሰዱት ዕርምጃዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጡ እና ድሃው የሕብረተሰብ ክፍል የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን መንግስት በውል ይገነዘባል።

ይህንን የሕብረተሰብ ክፍል ከጫና ለመታደግ በሚቀጥሉት ዓመታት መንግስት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራቸው የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥራዎች መካከል አንዱ የዋጋ ንረትን መግራት ይሆናል።

ውድ ኢትዮጵያውያን፥

ክቡራትና ክቡራን፥

የምናልመውና እንደ ግብ የምናስቀምጣቸው በጎ አላማዎች ትርጉም የሚኖራቸው ባለን የማስፈጸምና የማድረግ አቅም ነው። አዲሱ መንግስት የሚያስብ ፥ የሚያቅድ ፥ የሚከውን እንጂ ፥ በጎ የሚመኝ – ህልመኛ ብቻ ሊሆን አይገባም። እስከዛሬ ታቅደው ከጠረጴዛ ላይ ያልወረዱና ተጀምረው የተሰናከሉ ውጥኖቻችን ባለንበት የምንረግጥ እና አንዳንዴም ወደ ኋላ የምንንሸራተት አድርገውናል። በዜጎቻችን ላይ የሚደርስ ምሬት እና መንገላታትን ለመቅረፍ ፥ ጀምሮ የመጨረስ ባህልን በመላበስ ፥ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልፅና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ምቹ የሕዝብ አስተዳደር እንዲኖር አበክረን እንሠራለን። በተለይ በተለይ ሌብነትን እንደ ቀላል ድክመት ሳይሆን እንደ ከፍተኛ የደህንነትና የሕልውና አደጋ በማየት፥ በቀጣይ ዓመታት ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እንሠራበታለን።

ውድ የሀገሬ ልጆች፥

ክቡራትና ክቡራን፥

ባሳለፍነው የለውጥ ጉዞ ሰፋፊ ስኬቶች የነበሩ ቢሆንም በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋል። ፍትሕ ከሰፈነ ዕርቃናቸውን የሚቀሩ ፤ዴሞክራሲ ከተተከለ እስትንፋስ የማይኖራቸው ፥ እኩልነት ጭቆና የሚመስላቸው ፤ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ግለሰብና ቡድኖች አሁንም በሀገራችን ይገኛሉ ፤ ወደፊትም በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ሊደቅኑ የሚችሉት ፈተና ጨርሶ እንደማይጠፋ ልንገነዘብ ይገባል።

ባለፉት ድሎቻችን ላይ አከማችተን፥ ሥህተቶችን አርመን ፥ በአዳዲስ ሐሳብ ፥ በአዳዲስ እይታ ፥ ትውልዱን የሚመጥን አካሄድ ፥ ዘመኑን የሚዋጅ ቅኝት ይዘን ለመጭው ትውልድ የተሻለ ሀገር ለማስረከብ ተደምረን እንተጋለን። የምናመጣው ለውጥ ተቋማዊ መደላድልና ሕዝባዊ መሠረት ያለው እንዲሆን ስንሠራም ሆነ ለለውጥ ስንንቀሳቀስ አላማችን በጎ ቢሆንም አልፎ አልፎ ማጥፋትና መሳታችን አይቀርም። ሁሌም እንከን የለሽ ሥራ እንሠራለን የሚል መታበይ የለንም። ነገር ግን ከእኛ በኋላ የሚመጡትእኛ የሳትነውን እንደሚያርሙ፥የጀመርነውን እንደሚያጎለብቱሙሉእምነትና ተስፋ አለን። ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት፥ ባሳለፍነው የለውጥ ጉዞ የታዩ መልካም እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት እና ፍሬ የሚያፈሩበት ዘመን

ይሆናል።

በመጭዎቹ ዓመታት ዐቅማችንን በሚገባ ተጠቅመን አንድነታችንን የሚፈታተነውን ጥላቻ ፥ እንደ ኅዳር አህያ ሀብት ያለው ሁሉ የፈለግኩትን ካልጫንኳችሁ እያለ እንዲመኝ ያደረገውን ድህነታችንን እና ለጠላት ተጋላጭ የሚያደርገንን የውስጥ እና የውጭ ሁኔታ ተገዳድረን ድል ለማድረግ እንተጋለን። ጥላቻን በመግባባት ፥ ጭቆናን በዴሞክራሲ፥ ድህነትን በብልጽግና ፥ ለጠላት ተጋላጭነታችንን በጠንካራ ብሔራዊ የጸጥታ ኃይል ለመተካት ሁላችንም መረባረብ አለብን።

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፥

ክቡራትና ክቡራን፤

በመጨረሻም መጪዎቹ ዓመታት – “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ከአይበገሬነት ጋር የተሳሰረ መሆኑን የምናስመሰክርበት እንደሚሆን አልጠራጠርም። ፈተናዎች እንደሚያስፈነጥሩን እንጂ ፥ አስረው እንደማያስቀሩን የምናሳይበት ጊዜ ይሆናል። መጭዎቹ ዓመታት – ኢትዮጵያ ሰንኮፏን የምትነቅልበት ፥ ቁስሏን የምታክምበት፥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን በአለት ላይ የምታጸናበት፥ ገናናው ስሟ በሰፊው ዓለም የሚናኝበት ዘመን ይሆናል። በመጪዎቹ ዓመታት – የድህነት አከርካሪ ፥ የጥላቻ አንገት ፥ የመከፋፈል ወገብ ፥ የመፈናቀል ወሽመጥ ፥ የመገዳደል ክንድ ፥ በከንቱ የመወነጃጀል ጉልበት ፥ በሀገር ልጆች ብርቱ ትብብር ይሰበራሉ። አባቶቻችን “Akka duriifi harka xuriitti hin hafan” – “የቆሸሸ እጅና የትላንትደካማ ማንነት መጥራቱ አይቀርም” እንደሚሉት ፥ ፈተናዎች እንደ ወርቅ አንጥረው ያበሯት ሀገር ፥ የአቧራው ብዛትና የቆሻሻው ክምር ወርቅነቷን የማይለውጧት ኢትዮጵያ ትላንት ነበረች ፤ ዛሬም አለች። ነገ አቧራውን አራግፋና የቆሻሻውን ክምር ንዳ ስትነሣ ያኔ ከፊቷ የሚቆም ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል አይኖርም። ለዚህ ደግሞ አደራ አለብን። ዝናቡና ብርዱ ሳይበግራቸው ፥ ቁርና ፀሐይ ሳያማርራቸው ፥ በሌሊት እንቅልፍ ሳይሰንፉ ፤ ኢትዮጵያን ከመረጡ ዜጎቻችን የተሠጠን አደራ ፤ ለኢትዮጵያ መዳን ሲሉ ደማቸውን ካፈሰሱ ፥ ሕይወታቸውን ከገበሩ ውድ የሀገር ልጆች የተጣለብን አደራ ፤ ሌት ተቀን ስለ ኢትዮጵያ ሠላም በእንባ የሚማልዱ እናቶች ፥ እንዲሁም ከወዝና ላባቸው በጨለፉት ትጋት ሀገር ከሚያገለግሉ እናትና አባቶች የተላለፈልን አደራ ፥ እኛን ተስፋ አድርገው በኮልታፋ አንደበታቸው ስለ ኢትዮጵያ ከሚዘምሩ ልጆቻችን የተሰጠን አደራ አለብን። አዎ! ከባድ አደራ አለብን። ስለዚህም በቀጣይ ዓመታት የተጣለብንን አደራ ለመጠበቅና በላቀ ብቃት ለማስፈጸም እንደማናንቀላፋ ፥ ያለንን ሁሉ ያለስስት እንደምንሰጥ ፥ ለአፍታም እንደማንዘናጋ ፥ በዚህ አጋጣሚ ቃላችንን እንደምናድስ ፤ በመንግስታችን እና በፓርቲያችን ስም በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። አትጠራጠሩ – በቀጣዩ ዓመታት ተስፋችንን አጎልብተን ፥ ሥጋቶችን ቀርፈን ፥ ዕድሎችን አሟጠን ፥ ፈታኞቻችንን አሸንፈን ፥ ሀገራችንን

በብልፅግና ጎዳና የምናስኬድበት ዘመን ይሆናል።

ኢትዮጵያ በልጇቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

አመሰግናለሁ!

Galaatomaa!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!