መስከረም 18/2017 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀን 150 ሺሕ ኩንታል የማምረት አቅም ያለውን የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀመሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የመንግሥታችን በፍጥነት፣ በግዝፈት እና በንፅህና የመገንባት ጽኑ አቋማችን የማሳያ ነው ብለዋል። እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገራችን ያሉ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን 50 ከመቶ የሚያመርት ፋብሪካ እውን እንዲሆን የተሳተፋችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደዚህ ስፍራ ስመለስ የአመራር መርሆዎቻችን ማሳያ በሆነው በሥራው ፍጥነት ተደንቄያለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በመሰል ጠንካራ ሥራ መጪው ትውልድ ድህነትን እንደማይወርስ ይልቁንም ለእድገት እና ብልጽግና ጥሩ መደላድል እንደሚጠብቀው ያሳያል ብለዋል።
እንደ ለሚ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች በመላው ሀገራችን ካባዛን በሥራ ፈጠራ እና በሀገራዊ እድገት ላይ የሚኖረው የመባዛት ፍሬ አቻ የማይገኝለት ይሆናል፤ በተለይም በብረት ምርት፣ በማዳበሪያ ምርት ብሎም በሰፊው የኢንዱስትሪ እና ግብርና ልማት አብዮት የሚኖረው ተፅዕኖ ሰፊ ነው ሲሉም አክለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ ሀገራትን የሚገዳደሩ ፈተናዎች ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው መፍትሔዎችን ይሻሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የሚኖር የጋራ ትብብር እምቅ ሀብትና እድሎችን ለመጠቀም ብሎም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ ነው ብለዋል።
በመሰል ሥራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እንዲሁም ክብር ያለው አኗኗር እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላልም ነው ያሉት።