ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር ተወያዩ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የኮሪደር ልማት ስራ መሪዎች ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ከአንድ ወር በፊት የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጠቃላይ ግምገማ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የኮሪደር ልማት ስራ መሪዎች ጋር በድጋሚ በመገናኘት በስራዎቹ እርምጃ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

እነኚህ ስራዎቻችን የግንባታ ብቻ ጉዳዮች አይደሉም፤ ይልቁንም ከተማችንን ወደ ላቀ ምቹ፣ ንቁ እና ዘላቂ የመኖሪያ ከባቢ የመለወጥ ጥረቶች ናቸው ብለዋል።

ሥነ-ውበትን በማሳደግ፣ አረንጓዴነትን በማስፋት ብሎም መሰረተ ልማትን በማሻሻል የህዝባችንን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የስራ ዕድሎችንም እየፈጠርን ነው ሲሉም አክለዋል።

በጋራ እነዚህ ጥረቶቻችን የአዲስ አበባን አጠቃላይ ይዞታ በማላቅ እውነትም ለሁሉም ነዋሪዎቿ ፍላጎቶች የተመቸች ያደርጓታል ነው ያሉት።