ጤናን የሚጎዱ ምግብና መድኃኒት በማምረትና በማከፋፈል ላይ በነበሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ ምግብና መድሃኒትን በማምረትና በማከፋፈል ላይ የነበሩ ከ500 በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ድርጅቶች 388 በምግብ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ ከ120 የማያንሱት ደግሞ በመድሃኒት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።
ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው ለህብረተሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩ አራት ግለሰቦችም የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት ዓመት ለ4 ሺሕ 510 አዲስ የምግብ ዓይነቶች በመመዝገብ የገበያ ፈቃድ ተሰጥቷል።
ከዚህም ባሻገር ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን በላይ ምግብ ተገቢው ፍተሻ ተደርጎ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።
ሆኖም በ118 የምግብ ዓይነቶች ላይ በላብራቶሪ የጥራት ምርመራ ተደርጎ 67ቱ መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ለገበያ እንዳይቀርቡ መደረጉን ነው ያብራሩት።
ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለገበያ በማቅረብ በተጠረጠሩ ተቋማትና የምግብ ዓይነቶች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ከ247 የዱቄት፣ የካሳቫ ዱቄት፣ ማር፣ በርበሬ፣ ቅቤ ምርቶች ውስጥ 158 የሚሆኑት ባዕድ ነገር ተቀላቅሎባቸው በመገኘታቸው እንዲወገዱ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን 388 የምግብ አምራች ድርጅቶች እና ጅምላ አከፋፋዮች ላይ የማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ፈቃድ ስረዛና የእገዳ እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።
በባለስልጣኑ በተደረገው ቁጥጥር በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሊያደርስ የነበረ 670 ሺሕ ቶን ምግብ እንዲወገድ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በመድሃኒት ላይ በተደረገው ቁጥጥርም አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው 12 ሚሊየን 732 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የጥራት ደረጃን ያላሟሉ መድሃኒቶች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ መወገዳቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
መድሃኒቶቹ የተገኙባቸው 120 ተቋማት ላይም እንደ ጥፋት ደረጃቸው የማስጠንቀቂያ፣ የእገዳና የንግድ ፈቃድ ስረዛ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በህክምና መሳሪያዎችና በውበት መጠበቂያ ቁሶች ላይ በደረገው ቁጥጥርም በርካታ የጥራት ጉድለቶች በመገኘታቸው ባለስልጣኑ እርምጃ ወስዷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባለስልጣኑ ለመከላከያ ሰራዊትና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውቀዋል።