ጨፌ ኦሮሚያ ከነገ ጀምሮ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄዳል

መጋቢት 11/2014 (ዋልታ) ጨፌ ኦሮሚያ በነገው እለት አንደኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ 6ኛ የሥራ ዘመን ጉበኤውን ማካሄድ ይጀምራል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰኣዳ አብዱራህማን ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ምልዓተ ጉባኤው በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ጉባኤው ያለፉት 7 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ፣ ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ሦስት አዋጆች እና አንድ ደንብ ላይ መወያየት እንዲሁም የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።
ጉባኤው በነዚህ ጉዳዮች ሰፊ ውይይት እንደሚያደርግና በተይለም ደግሞ የክልሉ ሰላም እና መረጋጋት ዋና የትኩረት ማዕከል እንደሚሆን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችም ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ በገልማ አባገዳ አዳራሽ እንሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡
ሚልኪያስ አዱኛ (ከአዳማ)