ፈረንሳይ አካባቢ በተደረገ ፍተሻ በርካታ አደንዛዥ ዕፅ፣ መሳሪያዎችና የተለያዩ ቁሶች ተያዙ

ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) በየካ ክፍል ከተማ የፈረንሳይ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ፍተሻ በርካታ አደንዛዥ ዕፅና የአሸባሪውን መልዕክት የያዙ በራሪ ወረቀቶች፣ ቲሽርቶች እና የጦር መሳሪዎች እንዲሁም በርከት ያሉ የጸጥታ ኃይል አልባሳት መያዙን ገለጸ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት ባደረገ ፍተሻና ብርበራ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተለያዩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛል፡፡

የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ፍቃዱ ጽጌ ፖሊስ ጣቢያው በአራቱ ወረዳዎች ውስጥ በ15 ቤቶች ላይ ባደረገ ፍተሻ አንድ ሳጥን ሐሺሽ፣ ለሽብር ተግባር ቀስቃሽ የሆኑ በራሪ ወረቀቶች፣ የሽብርተኛው የትህነግን ተግባርን የሚያስተጋቡ ቲሸርቶ፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ፤የተለያዩ የጸጥታ ኃይሎች አልባሳት እና መድኃኒቶች መያዙን ገልፀዋል።

የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በሚደረስ ጥቆማና መረጃ መሰረት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን በተደረገ ፍተሻ በአንድ ግለሰብ ቤት ላይ ብቻ በርከት ያሉ የታሸገ እና የተተከለ ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ የተያዘ ሲሆን ግለሰቡም እንደሚጠቀምና እንደሚያከፋፍል ዋና ኢ/ር ፍቃዱ ጽጌ ገልፀዋል፡፡

የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪዎች ቦንብን ጨምሮ በፍተሻው እንደተያዙም ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ሃገርን ለማዳን የአሽባሪዎችን ስራ ለማጋለጥ እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን በመግለፅ ኅብረተሰቡ ለፖሊስ እየሰጠ ላለው ተጨባጭ መረጃ ኃላፊው ምስጋና ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።