ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 2 ሺሕ 400 መፃህፍት ለአብርኆት ቤተ መፃህፍት አበረከተ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የመጀመሪያ ዙር 2 ሺሕ 400 መፃህፍት ለአብርኆት ቤተ መፃህፍት ለግሷል።

የኮርፖሬቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ለአብርኆት ቤተ መፃህፍት ሁሉም አድማጭ ተመልካች መፃህፍት የማሰባሰብ ሂደቱን እንዲቀላቀል የማነሳሳት ስራ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።

በመጀመሪያው ዙር የመፃህፍት ማሰባሰብ ሂደትም ከቁጥር ይልቅ ለይዘት ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ መፃህፍት ትውልድን በመቅረፅ ሂደት አስትዋጽኦው ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ትውልዱ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ሀገርና ዓለምን ማወቅ ይፈልጋል እና በዚህ መልኩ የተሰባጠሩ የሳይንስ መፃህፍትን አካተናል ብለዋል፡፡

ሚሊዮን መፃህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 28  እስከ ግንቦት 29 2014 ዓ.ም የሚቆይ የመፃህፍት ማሰባሰብ መርሃግብር መጀመሩ ይታወቃል።

በመሆኑም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መፃኅፍት እንዲለግስና ትውልድን በማነፁ ሂደት አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ ቀርቧል።

በትዕግስት ዘላለም