ፎቶን ሞተርስ እና ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ሰኔ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) ፎቶን ሞተርስ እና ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ ፎቶን ሞተርስ 100 የከባድ ጭነት መኪኖችን ለኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አስረክቧል።

ስምምነቱን የቻይናው የፎቶን ሞተርስ የውጭ ንግድ ክፍል ፕሬዝዳንት ፉ ጅዊን እና የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሚካኤል ብዙአየሁ ተፈራርመዋል።

በቀጣይ የፎቶን ሞተርስ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርት እንደሚጀምርና ሙሉ የንግድ ተሽከርካሪዎችን ማለትም አውቶቡስ፣ ከባድ የጭነት መኪኖች፣ ቀላል መኪኖች፣ ሚኒትራኮች እና ሌሎችንም እዚሁ አምርቶ ገበያ ላይ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

የቻይናው ፎቶን ሞተርስ ግሩፕ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪኖች አቅርቦት ዘርፍ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየቱን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ባለፉት ቀናት ማሳወቁ ይታወሳል።

በአለምጸሃይ የኔዓለም