ፓርቲው ለሰሜኑ ግጭት በሰላም አማራጮች ዙሪያ ውይይት ማድረጉን ገለጸ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ በሰላም አማራጮች ዙሪያ ውይይት ማድረጉን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ይህን ሂደት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሰላም ለሀገሪቱ ልማትና ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑና ቀድሞውንም የፌዴራል መንግሥቱ ሳይፈልግ ተገዶ ወደ ጦርነቱ መግባቱን በማስታወስ ለሰላም ዕድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አምነው ሁለቱ ኮሚቴዎች ውሳኔውን ማሳለፋቸውን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የሰላም አማራጩ የመጨረሻ ግብ በተወሰነ መርህና ማዕቀፍ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሂደቱ ሕገ መንግሥታዊነትና ሕጋዊነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቅ እንዲሁም በአፍሪካ ኀብረት የሚመራ እንዲሆን አቋም መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ሰላም በአንድ ወገን የሚመጣ ባለመሆኑ ከሂደቱ በተፃራሪ በሌላኛው ወገን ለሚቃጣ ትንኮሳና ጥቃት ተገቢውን የአፀፋ እርምጃ ለመውሰድ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

ይህ የሰላም አካሄድ እንዲሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብና የኢትዮጵያ ወዳጆች ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ