ፓርኩን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተገለጸ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ሀሰን ፓርኩን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል ብለዋል።
ፓርኩ የውሀ አቅርቦትና መሰል የመሰረተ ልማት ጉድለቶች በተያዘለት ግዜ እንዳይጀምር እንቅፋት ሆኖበት መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመር የሚያስችል ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፓርኩ እስከ 135 የሚሆኑ ባለሀብቶችን ማስተናገድ የሚችልበት አቅም ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
በፓርኩ መዋእለነዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ልጅአለም አየለ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማድረግ እንዲሁም ጥራትን ለመጨመር የኦሮሚያ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሳይንሳዊ ምርምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቡልቡላ ፓርክም በሚፈለገው ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት እንዲቻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ የምግብ ጥራትና ደኅንነት ግብረ ኃይል ቡድን መሪ ጌታቸው ፈይሳ ፓርኩ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ማምረት እንዲችል በማሰብ የኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ከተባበሩት መንግሥታትን ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመሆን ለፓርኩ ግብአት ለሚያቀርቡ ዩኒየኖች እና ፋብሪካዎች ጥራት ለሚቆጠሩ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ስልጠናው በምርት ሂደት ውስጥ ዓለም ዐቀፍ ስታንዳርድን መከተል እንዲያስችል መሆኑ ተጠቁሞል።
በመስከረም ቸርነት