ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ 2 ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል አሉ

                                                       ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ

ጥር 13/2014 (ዋልታ) የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ 2 ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋት በመግለፅ የአኅጉሪቱን መሪዎች ንቅናቄ ተቀላቀሉ።

ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል የሚለውን ንቅናቄ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት እና የደቡብ አፍሪካው አቻቸው መጀምራቸው ሲታወስ በወቅቱ በግንባር ሆነው ዘመቻ ለኅብረብሔራዊ አንድነትን እየመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንቅናቄውን መቀላቀላቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።

አሁን ላይ ይህን ሐሳብ ደግፈው ብቅ ያሉት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የተባበሩት መንግሥታት በሚያደርገው ተቋማዊ ማሻሻያ በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ በትንሹ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎችን እስካላገኘች ድረስ መቀበል እንደሌለባት አስገንዝበዋል፡፡

አዳጊ አገራት ማሻሻያን መጠየቅ መብታቸው መሆኑን ሊታወቅ እንደሚገባም ከ10 የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በካምፓላ ባደረጉት ቆይታ መግልጻቸው ነው የተሰማው።

የአፍሪካዊያንን የፍትሓዊነት ጥያቄ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን መደገፋቸው ይታወሳል።

የአፍሪካ ኅብረት በመጪው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ 35ኛ የመሪዎች ጉባኤውን የሚያካሂድ ሲሆን ይህን አኅጉራዊ አጀንዳ ለምክክር ስለማቅረብ አለማቅረቡ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።