ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ‹‹የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ውጤቱን ስላየሁ አምንበታለሁ›› አሉ

                                                               ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጥር 13/2014 (ዋልታ) የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ቁልፍነት ስለማውቅ፣ ስለሰራሁበት፣ ውጤቱንም ስላየሁ አምንበታለሁ›› ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ማቋቋምያ አዋጅን ባለፈው ሳምንት ፈርሜያለሁ›› ያሉት ፕሬዝዳንቷ ‹‹መፈረም ኃላፊነቴ ቢሆንም የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ቁልፍነት ስለማውቅ፣ ስለሠራሁበት፣ ውጤቱንም ስላየሁ አምንበታለሁ›› ብለዋል፡፡

አገራዊ ምክክር በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር እንደሚደርግ ‹‹ሐሳብን በግድ መጫንን፣ ጦር መማዘዝን፣ ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ መጣልን ከመሳሰሉ አደጋዎች›› እንደሚያድንም አሳውቀዋል፡፡

‹‹የንግግር፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር አዲስ ባሕል ይፈጥራል፤ እንደ እኛ ከአውዳሚ ጦርነት ማግስት ለሚገኝ አገር ጠቀሜታው ግልጽ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ሲካሄድ የቆየው ጥቆማ ዛሬ ጥር 13 እንደሚያበቃ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለኮሚሽነርነት የተጠቆሙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁም ብለዋል፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ ምክክር ሂደት የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስም የተጠቆሙ ሴቶች ወደ ኋላ እንዳሉና እንዳፈሩ በማበረታታት ‹‹ትችላላችሁ›› ሲሉ አነቃቅተዋል፡፡