ፖሊስ ነገ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ይፋ አደረገ

መስከረም 23/2014 (ዋልታ) የኢፌዲሪ የመንግስት ምስረታ ፕሮግራም በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ለመታደም በርካታ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ ስለሚመጡ እንግዶች በአጀብ ሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ አሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የተለመደ ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክት ተላልፏል፡፡

የተለያዩ ሀገራት ፕሬዚዳንቶች ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ፣ የሀገራት ተወካዮች እንዲሁም የክልል ፕሬዚደንቶች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች በሚገኙበት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም የኢፌዲሪ መንግስት ይመሰረታል፡፡

የመንግስት ምስረታው በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም የኢሬቻ እና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ህብረተሰቡ በቅርቡ የተከበሩት የኢሬቻ እና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ እንዲሁም በአጠቃላይ ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ህዝቡ እንደሁል ጊዜው ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ላደረገው ቀና ትብብር እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸው በብቃት ለተውጡ የፀጥታ አካላት አመራሮችና አባላት የጋራ ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን እያቀረበ የመንግስት ምስረታው ፕሮግራሙ በውጤት እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሰረት የመንግስት ምስረታው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ

  1. ከሚያዚያ 27 አደባባይ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚ/ር
  2. ከአዋሬ በአዋሬ ገበያ ወደ ፓርላማ
  3. ከሴቶች አደባባይ ወደ ካሳንቺስ
  4. ከሴቶች አደባባይ በእንድራሴ ሆቴል ወደ ካሳንቺስ ቶታል
  5. ከ22 ወደ ቅዱስ ኡራኤል እንዲሁም ከኤድናሞል በአትላስ ሆቴል ወደ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን
  6. ከአትላስ ሆቴል በደሳለኝ ሆቴል ሩዋንዳ
  7. ከኤምፔሪያል ሆቴል ወደ ብራስ ሆስፒታል
  8. ከገርጂ ኮሪያ ሆስፒታል ውስጥ ውስጡን ወደ ብራስ ሆስፒታል
  9. ከጎሮ አዲሱ መንገድ መሄጃ ወደ ብራስ ሆስፒታል
  10. ከቦሌ ሚካኤል ወደ ቀለበት መንገድ እንዲሁም ከቦሌ ሚካኤል ወደ ሩዋንዳ ማዞሪያ
  11. ከካዲስኮ አደባባይ ወደ ቦሌ ሚካኤል ዋናው ቀለበት መንገድ
  12. ከቡልቡላ ወደ ቦሌ ሚካኤል
  13. ከመስቀል ፍላውር ወደ ጎርጎሪዮስ አደባባይ
  14. ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከጎተራ ወደ ወሎ ሰፈር አጎና ሲኒማ
  15. ከጎፋ ማዛሪያ አዲሱ መንገድ መስቀለኛ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያ ለገሃር
  16. ከቡልጋርያ ማዞሪያ ወደ ገንት ሆቴል እንዲሁም ከቡልጋርያ ማዞሪያ ወደ አፍሪካ ህብረት አደባባይ
  17. ከልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሜክሲኮ አደባባይ ወደ ለገሃር እንዲሁም ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ኑር ህንፃ በባልቻ መስቀለኛ ወደ አረቄ ፋብሪካ
  18. ከሞላ ማሩ ወደ ቅድስት ልደታ ቤተ-ክርስቲያን
  19. ከተክለ ሃይማኖት በርበሬ በረንዳ ወደ ዲ-አፍሪክ ሆቴል
  20. ከተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል
  21. ከአብነት ፈረሳኛ በቀድሞ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጎማ ቁጠባ ወደ ብሔራዊ ቴአትር
  22. ወሎ ሰፈር፣ ኦሎምፒያ፣ መስቀል አደባባይ ብሔራዊ ቤተ- መንግስት ግቢ ገብርኤል መታጠፊያ ሸራተን አዲስ አራት ኪሎ
  23. ጎርጎሪዮስ አደባባይ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም ፕሮግራሙ ተጀምሮ እስከሚጠናቅ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ፡፡

ፕሮግራሙ በሚካሄድበት መስቀል አደባባይ አካባቢ ከዛሬ መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ/ ጀምሮ በሁለቱም አቅጣጫዎች ግራና ቀኝ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ተሸከርካሪን አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት ግብረኃይል አስታውቋል፡፡

እንግዶች በአጀብ ሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ አሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የተለመደ ትብብር እንዲያደርጉ ግበረ ኃይሉ መልዕክቱን አስተላልፏል።