ፖሊስ ኮሚሽን ማህበረሰቡ ለፀጥታና ለደህንነት ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማህበረሰቡ መረጃ በመስጠትና ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ፡፡

የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ “ሰላምና ደህንነት” አስመልክቶ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ

ኮሚሽኑ በቅድሚያ ለታሪካዊው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያለ የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ላደረጋችሁት ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደተለመደው ሁሉ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ህጉንና የስነ-ምግባር ደንቡን አክብራችሁ እስከ አሁን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋፅኦ በማበርከታችሁ ኮሚሽኑ ምስጋናውን እያቀረበ በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከመጨረሻው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ኮሚሽኑ አጥብቆ ይጠይቃል።

የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆናችሁ ሌት ተቀን እያበረከታችሁት ላላችሁት አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ከልብ እያመሰገነ በቀጣይ ለሚኖረው የድምፅ አሰጣጥና አጠቃላይ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የተሰጣችሁን  ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነታችሁን  ልክ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ እንድትወጡ ከአደራ ጭምር ያሳስባል፡፡

ኮሚሽኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የፀዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና በድህረ-ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

ከዚህ አንፃር 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የሀገራችንን ታላቅነት ለመላው አለም የምናሳይበት ታላቅ ኩነት መሆኑንና ለገጽታችን ግንባታ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የተረዳው ኮሚሸኑ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ፀጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና የሁከትና ብጥብጥ መንስኤ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ በመረዳት ምንም ዓይነት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ በየትኛው አካባቢ እንዳይኖር ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የሀገራችን የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስምሪት ገብቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለህዝቡ እና ለስራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉት አስፈላጊ እና ወሳኝ የሆኑት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለ በቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኮሚሽኑ በአንክሮ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም መላው የሀገራችን ህዝብ እና የፀጥታ ሀይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንድንወጣ ጥሪያችንን በከፍተኛ አክብሮት እያቀረብን፤ በድምጽ መስጫ ዕለትና በድህረ-ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በህግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽን በጥብቅ ያስታውቃል፡፡

ኮሚሽኑ በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም አደረሳችሁ ይላል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ