ሚኒስቴሩ በ2 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ግብዓቶችን ለመቄዶንያ ለገሰ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – የገንዘብ ሚኒስቴር ግምታቸው 2 ሚሊየን ብር የሚሆኑ ግብዓቶችን ለመቄዶንያ የአዕምሮና አረጋዊያን መርጃ ማዕከል ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉ የኮንስትራከሽን፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ፣ የተሸከርካሪ ጎማዎች እና ምንጣፍን ያካተተ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ መንግስት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገልገል የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ አረጋዊያንንና የአዕምሮ ህሙማንን ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ይህንን አበረታች ተግባር ከመደገፍ አኳያ ማመስገን ብቻ ሳይሆን መንግስት ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

መቄዶኒያ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው”  በሚል መሪ ቃል በጀመረው ስራ ላይ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊተባበር ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ መሪ ቃሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም ላይ ለሚኖር ማንኛውም ማህበረሰብ ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ከመቄዶንያ ጎን በመሆን የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍ ማዕከሉ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እያስገነባ ላለው ባለ ሁለት ቤዝመንት 12 ፎቅ ህንጻ ግንባታ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

አክለውም ማዕከሉ በሀረር፣ በጎሬ፣ በአድዋ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከመንግስት የህንጻ ግንባታ ቦታዎችን ተቀብሎ ግንባታ የጀመረና በቀጣይ ከጎዳና በማንሳት አገልግሎት ሊሰጣቸው ካቀደው ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን ተረጂዎች የዛሬው ልገሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት ከጎናቸው ሆኖ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::