ኢትዮጵያ 400ሺህ የሚጠጋ የኮቪድ-19 ክትባት በቅርቡ እንደምታገኝ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ወደ 400ሺ የሚጠጋ የኮቪድ-19 ክትባት በቅርቡ እንደምታገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ባለው የኮቪድ-19 ክትባት እና በቀጣይ በሚሰጠው ሁለተኛው ዙር የክትባት መርሃ-ግብር ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቫይረሱን የመከላከል አቅም ከመተግበርና ከማስተግበር ጎን ለጎን ክትባቱን ለማግኘት እየተደረገ ያለውን ጥረት ዘርዝረዋል።

በዚህም መንግስት ለኮቪድ-19 ክትባት ግዢ ተጨማሪ ፋይናንስ በመመደብ ክትባቱን በአይነትም ሆነ በመጠን ለመጨመር ከአለም አቀፍ ድርጅቶችና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አያይዘውም የክትባቱን ተደራሽነት ለማስፋት ከሌሎች ድረጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም መሰረት 400ሺህ የሚጠጋ የኮቪድ-19 ተጨማሪ ክትባት በቅርቡ ከኮቫክስ አለም አቀፍ ጥምረት መምጣት እንደሚጀምር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።