የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ስራ ከጀመረበት ጀምሮ ለ3ሺህ አቤቱታዎች ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ስራ ከጀመረበት 1992 ዓ.ም ጀምሮ 5ሺህ 900 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ለ3ሺህ ያህሉ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ የሴቶችና ህፃናት ሕገ መንግስታዊ መብት እና የሕገ መንግስት ትርጉም ሚና ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባለት እና መንግስት ተቋማት የተውጣጡ የሴቶች ጉዳይ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አያካሄደ ነው።

በመድረኩም የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ስራ ከጀመረበት 1992 ዓ.ም ጀምሮ 5 ሺህ 900 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ውሳኔ የሰጠባቸው እና የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበባቸው መዝገቦች ብዛት 3ሺህ መድረሱ ተጠቁሟል።

102 ጉዳዮች የሕገመንግስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተከትሎ ደግሞ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦባቸው አብዛኞቹ መፅደቃቸውን አስታውቋል።

50 በመቶ የሚጠጉት ደግሞ የሴቶችና ህፃናትን መብት የጣሱ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በተያዘው ዓመት እስከ ሰኔ 2 ድረስ 518 አቤቱታዎችን መጣረቱን ተናግረዋል።

18 ጉዳዮች ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ለፌደሬሽን ምክር ቤት የተመሩ ሲሆን፣ 13 ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ እና 487 ያህሉ ደግሞ የሕገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ጉባኤው ለሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ ነው ያሉት ወ/ሮ መዓዛ፣ በቀጣይም ሴቶች በሚያቀርቡት አቤቱታ ላይ ብቻ ሳይሆን ለልማት፣ ለሰላም እና ለፍትህ ተደራሽነት ያደረጉት አስተዋጽኦ ላይም መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል።

(በትዕግስት ዘላለም)