የላሙ ወደብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በንግድ የሚያስተሳስር የኢኮኖሚ ኮሪደር ነው- አምባሳደር መለስ ዓለም

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – የላሙ ወደብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በንግድ የሚያስተሳስር የኢኮኖሚ ኮሪደር ነው ሲሉ በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ፡፡

የኬንያ ላፕሴት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን እና ቀጣናውን በንግድ በማስተሳሰር ሚናው የጎላ መሆኑን አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

የላሙ ክልል ምክትል ገዢ አብዱልከሪም አቡድ ብዋና ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን በሁለት አገር የሚኖሩ አንድ ዜጎች ናቸው ብለዋል፡፡ የላሙ ወደብ ግንባታ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናክረዋል ነው ያሉት፡፡

በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ እ.አ.አ በ2010 ጀምሮ በኬንያ ላሙ በመንግስት እየተገነባ ያለው የላሙ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቅቆ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተመርቆ በከፊል ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ የላሙ ወደብን በመጠቀም የወጭ ገቢ ንግዷን ማሳለጥ እንደሚያስችላት ከኢትዮጵያ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙኃን የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን በኬንያ የላሙ ወደብን በጎበኙበት ወቅት ተገልጿል፡፡

አገራቱን በምጣኔ ሀብት በማስተሳሰሩ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡

(በአስታርቃቸው ወልዴ)