የምግብና ስነ ምግብ ጤና ስትራቴጂና ፖሊሲን የሚያሳካ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው

ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – የምግብና ስነ ምግብ ጤና ስትራቴጂና ፖሊሲን ለማሳካት የሚያስችል ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ትግበራ መግባቱን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ጥናቱ በቅርቡ የፀደቀውን የቀጣይ 10 ዓመታት የምግብና ስነ-ምግብ ጤና ፖሊሲና ስትራቴጂን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ጥናቱን በዋናነት የሚፈፅሙ፣ የሚያስፈፅሙና የሚመሩ ከ500 በላይ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና የቤተ ሙከራ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የተግባር ልምምድ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጥናቱ የእናቶችና የህፃናት ጤናን ጨምሮ የስነ ምግብ ችግሮችን ከመሰረቱ ለማስወገድ የሚያግዝ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ጥናቱ ከ16 ሺህ በላይ አባወራዎችና ከ30 ሺህ በላይ ግለሰቦችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ለጥናቱ ማስፈጸሚያ 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

በጥናቱ ለሚሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ አጠናቃሪዎችና ተንታኝ ባለሙያዎች በቂ ሎጂስቲክስ መመደቡን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣት ሴቶች፣ እናቶችና መላው ማህበረሰብ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ማገዝ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በየዕለቱ የሚሰበሰበውን መረጃ በቀጥታ ወደ ማእከል የዳታ ቋት ለማስገባት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በኢንስቲትዩቱ የስነ ምግብ ምርምር ዳይሬክተርና የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ በበኩላቸው ጥናቱ በሁሉም ክልሎች ስር የሚገኙ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮችን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የምግብና ስነ ምግብ ስርዓትን ከመሰረቱ ለመቀየር የሚያስችል ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የመጀመሪያ ሀገራዊ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል።

ከእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ከስነ ምግብ ስርዓት ጋር ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ 16 በመቶ የሚሆነውን አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

“በዚህም በሀገሪቱ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የመቀንጨር ችግር፣ የቫይታሚን፣ የአይረንና የዚንክ እጥረትና ሌሎች ጤናና ጤና ነክ ችግሮች አሉባቸው” ብለዋል።

ሁሉንም የእድሜ ክልሎች የሚያማክለው ይህ ጥናት በቅርቡ የፀደቀውን የምግብና ስነ ምግብ ፖሊሲና ስትራቴጂን ለማስፈፀም የወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ የሚከናወን ሲሆን ለውጤታማነቱ ትክክለኛ ግብዓት ለማግኘት ጭምር የሚካሄድ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።