ሚኒስቴሩ ባህላዊ ህክምና በጤናው ዘርፉ ህጋዊ ስርዓት እንዲኖረው እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – ባህላዊ ህክምና በጤና ዘርፍ ውስጥ ህጋዊ ስርዓት ይዞ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የባህላዊ ህክምና ቡድን አስተባባሪ ወይዘሪት እህተማሪያም ሻምበል በኢትዮጵያ የባህላዊ ህክምና የቆየ ታሪክ ቢኖረውም በጤና ስርዓቱ ውስጥ ወጥ አሰራር ሳይዘረጋለት መቆየቱን ተናግረዋል።

ጤና ሚኒስቴር ዘርፉ ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ በህግና ስርዓት እንዲመራ ለማድረግ ቡድን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ዘርፉን የሚለከት የ10 ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፣ በእቅዱ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በግንዛቤ ማስፋት፣ የባህላዊ ህክምና አዋቂዎችን አቅም ማጎልበት፣ ተመራማሪዎችና የባህላዊ ህክምና አዋቂዎች አብረው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ጥናትና ምርምር ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች የምርምር ማዕከላት በዘርፉ የሚያደርጉትን ምርምር መደገፍ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ባህላዊ መድሃኒቶችን ከመጠቀም በፊት መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

ባህላዊ ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ ህጋዊ ሆኖ ምዝገባ የተጀመረው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን  እንደነበር አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ ባሉ ጊዜያት ዘርፉን ወጥ በሆነ ሥርዓት ከመምራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት የባህላዊ ህክምና የሚሰጡ አዋቂዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል አይታወቁም ብለዋል።

በመሆኑም መረጃ ማደራጀትና በዘርፉ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን መለየት በእቅዱ የአምስት ዓመት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ እንደተካተተ አንስተዋል።

የእቅዱ ተግባራዊነትም ባህላዊ ህክምና በጤና ዘርፉ ውስጥ ህጋዊ ስርአት ይዞ ቀጣይነት ባለው መልኩ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

60 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ የባህላዊ ህክምናን እንደሚጠቀም መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 90 በመቶ የሚጠጋ ህዝብ ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ ባህላዊ ህክምናን እንደሚጠቀም ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።