ህወሓት በሰነዘረው ጥቃት ውስጥ ድርሻ አላቸው ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ የድርጅቱ አባላት ላይ ክስ ሊመሰረት ነው


ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) –
ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ በሰነዘረው ጥቃት ውስጥ ድርሻ አላቸው ተብለው በመጠርጠራቸው በህግ ማስከበር ዘመቻው በቁጥጥር ስር የዋሉ የድርጅቱ አባላት ላይ ክስ ሊመሰረት ነው::
ህወሐት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡
በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ላይ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ ለመውጣት ሲጣጣሩ ነበሩ የተባሉት 42 ተጠርጣሪዎች በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ጸጋዬ አስታወቁ፡፡
አቶ ፈቃዱ 42ቱ ተጠርጣሪዎች በቀዳሚ ምርመራና በዋና ምርመራቸው ወቅት ጉዳያቸውን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡
ተጠርጣሪዎች ያልሆኑ ሰበባ ሰበቦችን በመቃረም የፍርድ ሂደቱ ዘገየ ለማስባል መሞከራቸውን ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ፣ በሕግ አግባብና በፍትህ መንገድ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ እንወጣለን በሚል ሒሳቦችን ሰርተው ከእስር ለመውጣትም ሲጣጣሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ምርመራው ከታሰበው በላይ በፍጥነት በመጠናቀቁ ይህ ስሌታቸው እንዳልሰራ ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሰሩት ልክ ሕግ ተገቢውን ፍርድ ይሰጣቸዋል ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ በቀጣዩ ሳምንት ተጠርጣሪዎቹ ለክስ እንደሚቀርቡ አመልክተዋል፡፡
ክሱ የወንጀል ክስ በመሆኑም ፍጥነቱ ምን ያህል ተቀናጅቶ እንደተሰራበት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በብዛት በምርመራና በሰበባሰበብ እንዲሁም በምስክር ማሰማት ሂደት ችግሮች ባያጋጥሙ ኖሮ ከዚህ ባነሰ ጊዜም ክሱ ይመሰረት እንደነበር ማሳወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡