ለፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ሊለማለት ነው

ፋሲል ከነማ

ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ሊያለማለት መሆኑ ተገለጸ።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደሩ የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድንን መረጃ ለደጋፊዎቹና ለማህበርሰቡ ባሉበት ለማድረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ከፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ስራ አስኪያጅና የቦርድ አመራሮች ጋር ቡድኑን የዲጂታል ፖርታል ባለቤት ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደሩ ከፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሊንክድኢን ከመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ከቴሌ ብር ጋር በማገናኘት አገልግሎት መስጠት የሚያስችልም ነው።

የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር በአንድ ወር ጊዜ አልመተን እናስረክባለንም ሲሉ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ጉዞ ወደ ሁሉም ዘርፎች ለማውረድ እንሰራለንም ብለዋል።

የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ባለሙያዎችን በማሟላት የመረጃ አስተዳደሩ ሳይቆራረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ የክለቡን ታሪክ፣ ዕለታዊ የእንቅስቃሴ መረጃ፣ የገቢ ማስገኛ ሽያጭ፣ የደጋፊዎች መረጃ፣ ድጋፍ ማሰባሰቢያና የመሳሰሉትን መረጃዎች አስተሳስሮ እንደሚይዝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።