በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለሚደረገው ጥረት በጥናትና በምርምር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ምክክር በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ለ“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደው የበይነ መረብ ውይይት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ያጋጠማት ወቅታዊ ችግር ወደ ዴሞክራሲ የሚደረጉ ሽግግሮች ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ ነው፡፡

ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ ከመገባቱ በፊት በርካታ የሰላም እድሎች ተፈጥረውለት ሊቀበል ያልቻለው የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን በተመሳሳይ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሰው፣ ቡድኑ ተኩስ አቁሙን በመጻረር ህጻናትን ሳይቀር ወደጦር ማሰለፍ መቀጠሉ ሊወገዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው የዘላቂ ሰላም ግንባታ የተፈጠሩ ችግሮችን ሳንፈታ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ተገደን ወደ ህግ ማስከበር የገባንበት ሂደት ወደ ዴሞክራሲ ለምናደርገው ሽግግር እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታይ በመሆኑ ለመፍታት የመላው ህዝብ ጥረትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ለውጡ ፈጣን በመሆኑ በሽግግር ላይ ያሉ ተመሳሳይ ሀገሮች ይህንን መሰል ተግዳሮት ያጋጠማቸው መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ ችግሩን በመፍታት ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሸጋገራቸውን አመለክተዋል፡፡

አክለውም የውጪ ጣልቃ ገብነት፣ የሂደት ጠመዝማዛ መሆን እና የሚዲያዎች አሉታዊ ሚና በሽግግር ሂደት እክል ሊፈጥሩ የሚችሉና በአንዳንድ ሀገሮችም የተፈጠሩ ለውጦች ረጅም ሂደት የጠየቁ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለውን ሰላም ከማስፈን አንጻር በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተከታታይ ውይይትና መግባባት የተደረሰበት ተግባራዊ ስራዎች ተጀምረው እንደነበር አስታውሰው፣ የሽብርተኛው ቡድን እነዚህን ወገኖች የተለያየ ስያሜ በመስጠት ለማሸማቀቅ የተደረጉ ዘመቻዎችንም አንስተዋል፡፡

“ዲፌንድ ኢትዮጵያ” ዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በበኩላቸው፣ ለሃገራቸው ሰላምና መረጋጋት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸው፣ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከመዋጋት በተጨማሪ ለሚገኙበት ሀገር የፓርላማ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ዳያስፖራውን በማስተባበር ሀገሩ ለምታቀርብለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንደሰጡ እንዲሁም በቀጣይነት ሊሰሩ ያቀዷቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም ወቅታዊ መረጃን በአግባቡ ለዳያስፖራው በጊዜው አለመድረስ ዳያስፖራው የተሳሳተ መረጃን እንዲይዝ ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡