ግብጽና ሱዳን የቅኝ ግዛት ስምምነትን ለማስጠበቅ ቢፍጨረጨሩም ኢትዮጵያ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ማሸነፏ አይቀርም – አቶ ሞቱማ መቃሳ

አቶ ሞቱማ መቃሳ

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – ግብጽና ሱዳን የቅኝ ግዛት ዘመን የዓባይ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀምን ለማስጠበቅ ቢፍጨረጨሩም ኢትዮጵያ በያዘችው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ማሸነፏ የማይቀር መሆኑን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ አስታወቁ፡፡

አቶ ሞቱማ እንደገለጹት፣ ግብጽና ሱዳን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት እንዲተገበር ቢፍጨረጨሩም ኢትዮጵያ በያዘችው እውነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ማሸነፏ አይቀርም፡፡

ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ለዓባይ ውሃ 86 በመቶ እንደምታበረክት፣ 65 ሚሊየን ህዝቧ በጨለማ ውስጥ እንደሚገኙ፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈራረቁባት ሀገር መሆኗንና በዓባይ የመልማትና የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት ጠፍቷቸው አይደለም ብለዋል::

እንደ ከዚህ በፊቱ ያለማንም ከልካይ ዓባይን መቶ በመቶ ሲጠቀሙ ኢትዮጵያና ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ከነድህነታቸው እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ የመፈለግ ዝንባሌ መሆኑንም ተናግረዋል:: ከዚህ በኋላ ይህ ጭራሽ የማይታሰብ መሆኑንም አመልክተዋል::

የዓባይ ውሃ የአፍሪካ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፤ በአፍሪካ ህብረት መፈታት ሲችል ግብጽና ሱዳን ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ መድረክ የመግፋትና የአለም መነጋገሪያ እንዲሆን ማድረግ የፈለጉበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እንደሆነ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡