ለምልምል ወታደሮች የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ለሚያቀርቡ አርቲስቶች ሽኝት ተደረገ

ነሐሴ 08/2013(ዋልታ) – በአዋሽና ጦላይ ማሰልጠኛ ጣቢያ ለሚሰለጥኑ ምልምል ወታደሮች የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ለሚያቀርቡ አርቲስቶች በብሔራዊ ትያትር ሽኝት ተደረገ።

በሽኝቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ባስተላለፉት መልዕክት ኪነ-ጥበብ የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት የራሷን አስተዋጽኦ ማድረጓን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የኪነ-ጥበብ ባለሙያው አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ “ጥበብ ለአገር አንድነት የበኩሏን ሚና ስትወጣ ቆይታለች” ብለዋል።

በጣሊያን የወረራ ዘመንም የህዝብን ሞራላዊ አንድነት በማነሳሳት ኢትዮጵያዊያን ድል እንዲቀዳጁ ለማድረግ ኪነ-ጥበብ የነበራትን ሚና አስታውሰዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል የህዝብን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ለማስቀጠል የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ የኪ-ጥበብ ባለሙያው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

“በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተጀመረው ተልዕኮ የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል።