ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ትግራይን ከህወሐት የሽብር ተግባር ለመታደግ ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ መሰረቱ

ነሐሴ 08/2013(ዋልታ) – የትግራይ ክልል ህዝብን ከሌሎች የኢትዮጵያ እህት ወንድሞቹ ለመነጠል አሸባሪው ህወሃት የሚያደርገውን ጥረት መመከትን ዓለማው ያደረገ  “ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ”  በይፋ ተመሰረተ።

የንቅናቄውን መመስረት አስመልክቶ አስተባባሪዎቹ አቶ ልዕላይ ሀይለማሪያም እና አቶ አታክልቲ ሃይለስላሴ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከአስተባባሪዎች መካከል አቶ ልዕላይ እንደገለጹት፤ “ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ” በትግራይ ክልል ተወላጆች የተመሰረተ ነው።

ንቅናቄው አሸባሪው ህወሃት የክልሉን ህዝብ ከኢትዮጵያ ለመነጠል የሚያደርገውን ጥረት ለመመከት የተመሰረተ ነው።

ኢትዮጵያዊ እሴቶችን መሰረት ያደረገው ንቅናቄው በአጭር፣ መካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚሰሩ እቅዶችን ማንገቡን ጠቁመው፤ አሸባሪው ህወሓት የተጋሩ ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ወደ ውስብስብ ፖለቲካ ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን  ያብራሩት አቶ ሊላይ፤ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለውና ኢትዮጵያን ለመገንባት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የራሱን አሻራ ያሳረፈ ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እቅድ እንዳለው በማኒፌስቶው ጭምር ያስቀመጠ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ላላይ፤ “ይህ እንዲሆን መፍቀድ በትግራይ ህዝብ ላይ ክህደት መፈጸም ነው” ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ መፈጸሙን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ የትግራይ ክልል ህዝብን ለማስጨረስ በአጎራባች ክልሎች ላይ ትንኮሳ በመፈጸም ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል።

ህፃናትን በጦርነት እየማገደ ያለው አሸባሪው ህወሓት “ከጥንት ጀምሮ የባንዳነት ተልዕኮ ያለው በመሆኑ የትግራይን ህዝብ አይወክልም” ብለዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታት “ራዕይ የተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ” መመስረቱን ይፋ አድርገዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የሽብር ቡድኑ አባላትና ተላላኪዎች “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” በማለት በማደናገር ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ “እነዚህ ሰዎች የትግራይን ህዝብ ፍፁም ሊወክሉ የማይችሉ ናቸው” ብለዋል።

ሌላው አስተባባሪ አቶ አታክልቲ ሃይለስላሴ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ ንቅናቄው የተመሰረተው ኢትዮጵያዊ እሴቶችን መሰረት ያደረገ፣ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር ባህልና እሴት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።

ከየትኛውም የሃይማኖትና የፖለቲካ ፖርቲ ነጻ የሆነ ንቅናቄ መሆኑን ገልፀው፤ “ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ንቅናቄውን በመቀላቀል የሽብር ቡድኑን በጋራ መታገል ይገባናል” ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።